የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ስማርት አዲስ አበባን በመፍጠር እመርታዊ ውጤት እያስገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ስማርት አዲስ አበባን በመፍጠር እመርታዊ ውጤት እያስገኘ ነው
አዲስ አበባ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ስማርት አዲስ አበባን በመገንባት እመርታዊ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ገለጸ።
በአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ አስተባባሪነት ችግር ፈቺ አሰራሮችን በነፃ በማልማት የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት እንዲጠቀሙ ያደረጉ የግል ተቋማትና ባለሙያዎች የእውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አዋሌ መሀመድ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ አሰራሮችን ላበለፀጉ ለአምስት ተቋማትና ዘጠኝ ባለሙያዎች እውቅና ተሰጥቷል።
ስማርት ሲቲ አዲስ አበባን በመገንባት ሂደት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎታቸውን ለበጎ ዓላማ በማዋል ድጋፍ ላደረጉ የግል ተቋማትና ሙያተኞች ምስጋና አቅርበዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገው የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂም በስማርት ሲቲ ትግበራ አዲስ አበባን በመገንባት እመርታዊ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የአዲስ አበባ ተቋማት ለተገልጋዮች ፈጣንና ቀልጣፋ የዲጂታል አገልግሎት በመስጠት ዕድገትን የሚያሳልጥ ፈጣን የለውጥ ምኅዳር መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የስማርት ሲቲ እሳቤና ግንባታ ከተማዋን ለነዋሪዎችና ጎብኚዎች ምቹ እያደረጉ ነው ብለዋል።
የስማርት ሲቲ ትግበራ ትብብርን የሚጠይቅ መሆኑን አንስተው፤ ዛሬ እውቅና ያገኙ አካላትም የተቋማትን ችግር በመፍታት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል ተግባር ማከናወናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም አዲስ አበባ ያላትን ፀጋ ተጠቅማ ወደ ተሻለ ደረጃ እንድትሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግርና ሌሎች የለውጥ ስራዎች ላይ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዕውቅና ካገኙት መካከል የሜድኮ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ከፍተኛ ፕሮጀክት አስተዳደር አቤል ደረጄ እንዳለው፤ የከነማ ፋርማሲ አሰራርን የሚያዘምንና የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሲስተም አበልፅጓል።
ከጓደኛው ጋር በመሆን የመስሪያ ቦታ አሰጣጥ ስርዓቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል የሚቀይር ዘመናዊ የፈጠራ ሥራ አበርክተናል ያለው ደግሞ ጌታቢል መንግስቱ ነው።
ሁሉም ህብረተሰብ ባለው አቅም ሀገሩን ለማሳደግ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ወጣቶቹ ጥሪ አቅርበዋል።