ቀጥታ፡

የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሁሉም የኢኮኖሚ አመላካቾች የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል ታሳቢ ያደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሁሉም የኢኮኖሚ አመላካቾች የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ 25ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት የበጀት መግለጫ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡


 

ምክር ቤቱም በቀረበው የ2019 የበጀት መግለጫ ላይ ከተወያየ በኋላ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መርቶታል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ለምክር ቤት ባቀረቡት የ2019 በጀት ዓመት የበጀት መግለጫ እንደገለጹት፤ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውና የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ትግበራ ስኬታማ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን በብቃት በመቋቋም ጠንካራ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ገልጸው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አበርክቶ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከ2012 እስከ 2016 ባሉት የበጀት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ በየዓመቱ የ6 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ እንደነበር በማስታወስ፤ በ2017 በጀት ዓመት የ9 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ በዘንድሮው በጀት ዓመት የመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረውን ዓለም አቀፍ ጫና ጭምር በመቋቋም የ10 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ታስመዘግባለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ተርታ የሚያሰልፋትን ስኬት ማስመዝገቧን ገልጸው፤ ይህም የተቀናጀ የገንዘብና ፊሲካል ፖሊሲው ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


 

ይሄውም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የሸቀጦችን የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አሃዝ ማውረድ አስችሏል ብለዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የኢኮኖሚ አፈጻጸሙ በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ በማንሳት፤ ስኬቱ የተረጋጋና የበለጸገ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡

የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትም በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሁሉም የኢኮኖሚ አመላካቾች የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

በ2019 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 10 ነጥብ 1 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ እንደሚጠበቅና የቀረበው ረቂቅ በጀትም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተሳካ ሁኔታ ገቢራዊ ለማድረግና የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት የሚፈጥረውን የኢኮኖሚ ጫና ጨምሮ የውጭ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ለመቋቋም ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የፌደራል መንግስትን ጠቅላላ ገቢ 1 ነጥብ 817 ትሪሊየን ብር ለማድረስ ታሳቢ መደረጉን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 6 ትሪሊየን ብር የሚሆነው ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ለመሰብሰብ መታቀዱን አመላክተዋል።

ለ2019 በጀት ዓመት የቀረበው አጠቃላይ 2 ነጥብ 339 ትሪሊየን ብር በጀት ከዘንድሮው በጀት ዓመት አንጻር የ21 ነጥብ 3 በመቶ እድገት እንዳለው ገልጸዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለያዩ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገቧን ገልጸዋል፡፡

ሪፎርሙ የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲወሰን በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ማሳደግ፣ የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሃዝ መውረድና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ማሳደግ አስችሏል ብለዋል፡፡

ለ2019 በጀት ዓመት የቀረበው ረቂቅ በጀት ከባለፈው ዓመት የላቀ መሆኑ የመንግሥትን ግዙፍ የልማት ዕቅዶች ለማሳካት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም