ቀጥታ፡

በክልሉ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከተሞች ገጽታቸው እየተቀየረ ነው

ዲላ ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተሞችን በህብረተሰብ ተሳትፎ ገጽታቸውን በመቀየር ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ 100 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ የመሠረተ ልማቶች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በመቀናጀት በሚያከናውናቸው ተግባራት የከተሞች የተጎሳቆለ ገጽታ እየተቀየረ ነው ብለዋል።


 

ዛሬ በይርጋጨፌ ከተማ ለአገልግሎት የበቁ መሠረተ ልማቶች የዚሁ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በከተማው በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ ልማት የተጀመሩ መሠረተ ልማቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና የውስጥ አቅምን አስተባብሮ ብልጽግናን የማረጋገጥ ሥራ መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

በከተማው ሰው ተኮር የሆኑ ልማት ስራዎች ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን ጠቁመው በመኖሪያ ቤት አቅርቦት በኩል እየተከናወነ ያለው ስራም ተጠቃሽ መሆኑን አመልክተዋል ።

በዞኑ ከተሞችን ውብና ጽዱ እንዲሁም ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ ከማድረግ አንጻር ውጤታማ ተግባር መከናወኑን ያነሱት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ናቸው።


 

በዞኑ በሚገኙ ከተሞች የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ ይገኛል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ከተሞችን ፅዱና ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ ብዙአየሁ ታደሰ በበኩላቸው ፤ በህብረተሰብ ተሳትፎ ለአገልግሎት የበቁት የመሠረተ ልማት ተቋማት ለህብረተሰቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ናቸው ብለዋል።


 

ዛሬ ለአገልግሎት የበቁ መሰረተልማቶች  የሌማት ትሩፋት ምርቶች መሸጫ ሼዶች፣ ድልድይ፣ መማርያ ክፍሎች እንዲሁም 40 መኖርያ ቤቶችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመው ለመሰረተ ልማቶቹ ግንባታ 100 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን አንስተዋል።

በከተማዋ መሶብ አንድ ማዕከልና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራ እየተፋጠነ እንደሚገኝና በቀጣይ ወር ለአገልግሎት እንደሚበቁ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም