ቀጥታ፡

ዓለም ዋንጫን የሚያስተናግዱት 16 ስታዲየሞች 

በሙሴ መለሰ

23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ በአሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ ጣምራ አዘጋጅነት ዛሬ በይፋ ይጀምራል። 

ይህ ውድድር በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የ32 ሀገራትን ቁጥር በማሳደግ 48 ሀገራት ተሳታፊ የሚሆኑበት ታላቅ መድረክ ነው። 

ውድድሩ በሶስቱ ሰሜን አሜሪካ ሀገራት በሚገኙ 16 ከተሞች ውስጥ በተመረጡ 16 ስታዲየሞች የሚካሄድ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ውድድሩን የሚያስተናግድ አንድ አንድ ስታዲየም ብቻ ተዘጋጅቷል።

ጨዋታዎቹን በደመቀ ሁኔታ ለማስተናገድ የተመረጡት ስታዲየሞችም፦

በአሜሪካ የሚገኙ ስታዲየሞች

1. ሜትላይፍ ስታዲየም (ኒው ዮርክ/ኒው ጀርሲ) 

እ.አ.አ በ2010 ስራ የጀመረው ይህ ስታዲየም 82,500 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። ስታዲየሙ እጅግ በጉጉት የሚጠበቀውን የፍጻሜ ጨዋታ ጨምሮ በአጠቃላይ 8 ጨዋታዎችን ይካሄድበታል። 

2. ኤቲ ኤንድ ቲ ስታዲየም (ዳላስ፣ ቴክሳስ) 

እ.አ.አ በ2009 አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህ ስታዲየም 94,300 ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን፣ ከውድድሩ ስታዲየሞች ሁሉ በትልቅነቱ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

በአጠቃላይ 9 ጨዋታዎችን በማስተናገድ ከሁሉም ስታዲየሞች በርካታ ጨዋታዎች የሚደረጉበት ስታዲየም ነው።

3. ሶፊ ስታዲየም (ሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ)

 እ.አ.አ በ2020  የተገነባውና ዘመናዊው ሶፊ ስታዲየም 70 ሺህ 240 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። የአዘጋጇ አሜሪካ ብሔራዊ ቡድን ከፓራጓይ ጋር የሚያደርገውን የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ጨምሮ ስምንት ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።

4.  ሜርሴዲስ ቤንዝ ስታዲየም (አትላንታ፣ ጆርጂያ) 

እ.አ.አ በ2017 ስራ የጀመረው ይህ ስታዲየም 71 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። ስታዲየሙ ለአለም ዋንጫው ማጠናቀቂያ ወሳኝ ከሆኑት ጨዋታዎች አንዱ የሆነውን የአንዱን ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ጨምሮ በአጠቃላይ 8 ጨዋታዎችን እንዲያስተናግድ ተመርጧል።

5.   ሃርድ ሮክ ስታዲየም (ሚያሚ፣ ፍሎሪዳ) 

እ.አ.አ በ1987 የተገነባውና ረጅም አገልግሎት የሰጠው ሃርድ ሮክ ስታዲየም 64,767 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። ይህ ስታዲየም የደረጃ ጨዋታን ጨምሮ 7 ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።

6.   አሮው ሄድ ስታዲየም (ካንሳስ ሲቲ፣ ሚዙሪ) 

እ.አ.አ በ1972 ስራ የጀመረውና አንጋፋው አሮው ሄድ ስታዲየም 76 ሺህ 416 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፣ በውድድሩ ወቅት 6 ጨዋታዎችን በስታዲየሙ ለማካሄድ ዝግጅቱን አጠናቋል።

7.   ኤንአርጂ ስታዲየም (ሂውስተን፣ ቴክሳስ)፦ 
እ.አ.አ በ2002 ስራ የጀመረው ኤንአርጂ ስታዲየም 72 ሺህ 220 ተመልካቾችን የመያዝ ከፍተኛ አቅም ያለው ሲሆን፣ በአጠቃላይ 7 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።

8.   ጂሌት ስታዲየም (ቦስተን፣ ማሳቹሴትስ)

 እ.አ.አ በ2002 ዓ.ም ስራ የጀመረውና በስፖርቱ አለም ታዋቂ የሆነው ጂሌት ስታዲየም 65,878 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፣ 7 ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ተመርጧል።

9.   ሊንከን ፋይናንሻል ፊልድ ስታዲየም (ፊላዴልፊያ፣ ፔንስልቬንያ)

 እ.አ.አ በ2003  ስራ የጀመረው ይህ ስታዲየም 67,594 ተመልካቾችን በስታዲየሙ ማስተናገድ የሚችል ሲሆን፣ 6 ጨዋታዎችን እንደሚያስተናግድ ታውቋል።

10.   ሉመን ፊልድ ስታዲየም (ሲያትል፣ ዋሽንግተን)

እ.አ.አ በ2002 ስራ የጀመረው ሉመን ፊልድ ስታዲየም 69 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። ስታዲየሙ በውድድሩ ወቅት 6 ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።

11.   ሌቪስ ስታዲየም (ሳን ፍራንሲስኮ፣ ካሊፎርኒያ)

እ.አ.አ በ2014 ወደ አገልግሎት የገባው ሌቪስ ስታዲየም 68,500 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፣ በአጠቃላይ 6 ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ ሆኗል።

በሜክሲኮ የሚገኙ ስታዲየሞች 

12. አዜቴካ ስታዲየም (ሜክሲኮ ሲቲ)፦ እ.አ.አ በ1966 ዓ.ም ስራ የጀመረውና ታሪካዊ ስታዲየም አዜቴካ ስታዲየም፣ ለዚህ ዓለም ዋንጫ ከፍተኛ እድሳት ተደርጎለታል።

በአሁኑ ወቅት 87 ሺህ 523 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፣ መላው ዓለም በጉጉት የሚጠብቀውን የዓለም ዋንጫውን የመክፈቻ ጨዋታ ጨምሮ 5 ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።

አዜቴካ ስታዲየም (Estadio Azteca) የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ በማስተናገድ በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ሶስት የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታዎችን ያስተናገደ ብቸኛው ስታዲየም የመሆን አዲስ ታሪክ ይሰራል። 

13.  ቢቢቪኤ ስታዲየም (ሞንቴሬይ)

እ.አ.አ በ2015 የተመረቀው ዘመናዊው ቢቢቪኤ ስታዲየም 53,500 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፣ በአጠቃላይ 4 ጨዋታዎች ይደረጉበታል። 

14.  አክሮን ስታዲየም (ጓድላሀራ)

እ.አ.አ በ2010 ዓ.ም ስራ የጀመረው አክሮን ስታዲየም 48,071 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፣ በውድድሩ ወቅት 4 ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።

በካናዳ የሚገኙ ስታዲየሞች 

15. ቢሲ ፕሌስ ስታዲየም (ቫንኩቨር)

እ.አ.አ በ1983 ስራ የጀመረውና እ.አ.አ በ2011 ዘመናዊ እድሳት የተደረገለት ቢሲ ፕሌስ ስታዲየም 54,500 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። ይህ ስታዲየም 7 ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።

16. ቶሮንቶ ስታዲየም (ቶሮንቶ)

እ.አ.አ በ2007  ስራ የጀመረው ይህ ስታዲየም ለዓለም ዋንጫው ዝግጅት ሲባል የመቀመጫ ቁጥሩ እንዲጨምር ተደርጓል። 

ስታዲየሙ 45,000 ተመልካቾችን የሚይዝ ሲሆን ይህም ከሁሉም የውድድሩ ስታዲየሞች በመያዝ አቅሙ ትንሹ ያደርገዋል። 

የካናዳ ብሔራዊ ቡድን የሚያደርገውን የመጀመሪያ ጨዋታ ጨምሮ 6 ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።

ከአጠቃላይ 104 ጨዋታዎች ውስጥ አሜሪካ 78 ጨዋታዎችን፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ በተመሳሰይ 13 ጨዋታዎችን ያስተናግዳሉ።

ለዓለም ዋንጫው ዝግጅት ብቻ በ16ቱም ስታዲየሞች ላይ ለተደረጉ ማሻሻያዎች (ሜዳዎችን ከተፈጥሮ ሳር ጋር ማላመድ፣ የክብር እንግዶች መቀመጫዎችን ማደስ እና የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን መዘርጋትን ጨምሮ) በአጠቃላይ ከ1 ቢሊዮን እስከ 1.5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ወጪ እንደወጣ ይገመታል።

ይህ ቁጥር ከቀደሙት ዓለም ዋንጫዎች (ለምሳሌ በኳታር ስተናጋጅነት በተካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ 200 ቢሊዮን ዶላር) አንጻር በጣም ያነሰ ሲሆን ይህም የሆነበት ምክንያት አዳዲስ ስታዲየሞች ባለመገንባታቸው እና ሁሉም ስታዲየሞች አስቀድመው ዝግጁ የነበሩ በመሆናቸው ነው።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም