በክልሉ ዘመናዊ የመንግስት አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ዘመናዊ የመንግስት አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ዲላ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ የመንግስት አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ ውጤታማ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
የዲላ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዛሬ በርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጥላሁን ከበደ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ማዕከሉ በክልሉ ሦስተኛው ሲሆን ብዝሃ አገልግሎቶችን በማቀፍ ለማህበረሰቡ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችልም ተመላክቷል።
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዚህ ወቅቱ እንዳሉት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰራርን ከማዘመን ባለፈ የአገልጋይነት ባህል የሚገነባና የተገልጋይ እርካታን የሚያሻሽል ነው።
በተለይ ብዝሀነት ባለበት እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዜጎችን እንግልት በመቀነስ ረገድ ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።
በክልሉ ዘመናዊ የመንግስት አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ ውጤታማ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
የለውጡ መንግስት ዘመናዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ከአንድ ማዕከል አገልግሎት እስከ ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም የደረሰ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን ያነሱት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ናቸው።
በማዕከሉ በአራት የፌደራል እና በአምስት የክልል ተቋማት የሚሰጡ 32 የተለያዩ የአገልግሎት አይነቶች ይሰጣሉ ብለዋል።
ይህም በአንድ ማዕከል የዜጎችን ክብር በጠበቀ መልኩ ብዙ አገልግሎቶችን ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረው፣ መሰል አገልግሎቶችን የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በክልሉ ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የዲላ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በወላይታ ሶዶ እና በአርባ ምንጭ ከተሞች ከተገነቡት ቀጥሎ ሦስተኛው መሆኑ ታውቋል።