ቀጥታ፡

በክልሉ የዘር ጥራትና መጠንን በማላቅ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው

ወላይታ ሶዶ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ዘር በዓይነት፣ በመጠንና በወቅቱ በማቅረብ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዘርፍ እና በክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የዘር ብዜት ዕቅድ አፈጻጸምና ዝግጅት ላይ ያተኮረ የባለ ድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።


 

በመድረኩ የተገኙት የቢሮው ምክትል ኃላፊና የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ግዳልቅ አልቅሚ እንደገለጹት፤ በክልሉ የዘር ጥራትና መጠንን በማላቅ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል።

ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ ለኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓትን ለማቅረብና የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ለዚህ ስኬት ደግሞ የዘር አቅርቦትን በዓይነት፣ በመጠንና በወቅቱ ማሟላት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በ2017/18 የምርት ዘመን በክልሉ ከ2 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ማምረት መቻሉንም ገልጸዋል።

የአርሶ አደሮችን የዘር ፍላጎት በማሟላት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

ለዚህም ማነቆዎችን በጋራ በመፍታት የዘር ብዜት አስተዳደርን ማጠናከር እንደሚገባ ነው የተናገሩት።


 

የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ያሲን ጎአ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚገኙ የምርምር ማዕከላትን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ዘር በማባዛት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የአርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

የምርጥ ዘር ብዜቱ ዓላማ የጥራጥሬ፣ የስራ ስር ሰብሎችንና የፍራፍሬዎች እንዲሁም የዓሳና የእንስሳት ዝርያዎችን በውጤታማነት በመከወን የክልሉን ፍላጎት ተደራሽ ማድረግ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህን ለማስቀጠል ደግሞ ከክልሉ ግብርና ቢሮ እንዲሁም ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ቅንጅት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም