በፓርኩ የአዳዲስ ኩባንያዎች ተሳትፎ ማደጉ የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት እየጨመረው ነው - ኢዜአ አማርኛ
በፓርኩ የአዳዲስ ኩባንያዎች ተሳትፎ ማደጉ የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት እየጨመረው ነው
ሀዋሳ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ የአዳዲስ ኩባንያዎችን ተሳትፎ በማሳደግ የዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት እንዲጨምር መደረጉን የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀይሉ የተራ እንደገለጹት፤ በፓርኩ የሀይል አቅርቦትና የፍሳሽ ማጣሪያን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች መሟላታቸው ባለሀብቱን እየሳበ ነው።
በዚህም በፓርኩ የዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትና የውጭ ምንዛሬ ግኝት የሚያጠናክሩ አዳዲስ ኩባንያዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው፣ ቡናና ሙዝ ማቀነባበርን ጨምሮ በአዳዲስ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎች ወደስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም የሙዝ ምርትን ወደችብስነት መቀየርና ቡናን በቀጥታ አቀነባብሮ ወደውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ኩባንያዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣በሥራ ዕድል ፈጠራና በገበያ ትስስር ልዩ ዕድል ይዘው የመጡ ናቸው ብለዋል።
በፓርኩ አዲስ ወደስራ ከገቡ ኩባንያዎች መካከል የ"ኤፔክስ ማኑፋክቸርንግና ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት" መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ተፈራ፣ ድርጅቱ የሙዝ ምርትን በማቀነባበር ችፕስ እያመረተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ200 በላይ ዜጎች በድርጅቱ ቋሚ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ገልጸው፣ በሲዳማና አጎራባች አካባቢዎች ለሚገኙ የሙዝ አምራች አርሶ አደሮችም የገበያ ትስስር ተፈጥሯል ብለዋል።
አቶ መስፍን እንዳሉት ድርጅቱ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ዘንድሮ ወደስራ የገባ ሲሆን በቀን እስከ 20 ሺህ ኪሎ ግራም ሙዝ በመፍጨት ወደችፕስነት በመቀየር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባል።
በፓርኩ በዘንድሮ ዓመት ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት ወደስራ የገባው የቻይናው የመይመይ የቡና ፕሮሰሲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ተወካይ ሚስተር ጄይ ሴን በበኩላቸው፤ በፓርኩ ውስጥ ለሥራ ምቹ ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል።
ድርጅቱ ቡናን ከአርሶ አደሩ ማሳ በቀጥታ ተቀብሎና አቀነባብሮ በቀጥታ ለዓለም አቀፍ ገበያ እንደሚያቀርብ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅትም ወደተግባር እየገባ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በቡና ልማት የተሰማሩ በርካታ አርሶ አደሮችን ካቀፉ 10 ማህበራት ጋር የገበያ ትስስር መፍጠሩን የገለጹት ሚስተር ጄይ፣ ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ ሲንቀሳቀስ ከ750 ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በኩባንያዎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ዶክተር ታምር ጌታቸው እና ወይዘሮ ራሔል አስናቀ በፋብሪካዎች በመቀጠር የስራ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።
በ2012 ዓም ወደሥራ የገባው ይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ294 ሄክታር መሬት ያረፈ ሲሆን አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችም የተዘረጉለት ነው።
ፓርኩ አዳዲስ ኩባንያዎችን በመሳብ እና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ አበረታች ውጤት እያስገኘ ሲሆን ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ እድገትም ትልቅ አቅም ይፈጥራል።