ኮሌጁ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው የተሻሻሉ ችግኞችን በማዘጋጀት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮሌጁ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው የተሻሻሉ ችግኞችን በማዘጋጀት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው
ሚዛን አማን፣ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፡-የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚሆኑና የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው የተሻሻሉ ችግኞችን በማዘጋጀት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ።
ኮሌጁ የማኅበረሰብ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ለማስፋፋት በጥናትና ምርምር የታገዘ ሥራ እያከናወነ መሆኑንም አስታውቋል።
የኮሌጁ ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን አለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኮሌጁ በአረንጓዴ ልማት ሥራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ ችግኞችን በማዘጋጀት ለማኅበረሰቡ እያሰራጨ ነው።
በተለይ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ውጤታማነት ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዘንድሮ ተከላ ከ250 ሺህ በላይ በምርምር የተደገፉና የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን አዘጋጅቷል ብለዋል።
ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል ከዛፍ ጋር ትስስር ያላቸው ቁንዶ በርበሬ እና ቡናን ጨምሮ የሻይ ቅመም፣ የፍራፍሬ፣ የውበትና የጥላ ዛፎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
የችግኝ ዝርያዎቹ ፈጥነው እንዲደርሱ፣ በሽታ እንዲቋቋሙና ምርታማነታቸው የተሻለ እንዲሆን ኮሌጁ ከተለያዩ የግብርና ምርምር ማዕከላት ጋር በትብብር ሲሰራ መቆየቱንም አቶ ጥላሁን አክለዋል።
የተዘጋጀውን ችግኝ ለማህበረሰቡ ከማሰራጨት ባሻገር ኮሌጁ በራሱ እንደሚተክል ገልጸው በዚህም የውስጥ ገቢውን ከማሳደግ ባለፈ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር በምግብ ራስን ለመቻልና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አመልክተዋል።
በኮሌጁ ችግኝ ጣቢያ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው እየሰሩ ካሉ ወጣቶች መካከል መሠረት ታፈሰ በችግኝ ጣቢያው በዘርፉ ባለሙያዎች ታግዛ በመሥራት የቀሰመችው ሙያ በራሷ ችግኝ የማዘጋጀት አቅምን ለማጎልበት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላት ገልጻለች።
የተዘጋጁ ችግኞችን የመከታተልና የመንከባከብ ሥራ በመሥራት ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ እልፍነሽ ተገኝ እና ታጋይነሽ ዘውዴ ናቸው።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከተጀመረ ወዲህ ኮሌጁ ችግኞችን በብዛት እያዘጋጀ በመሆኑ ዓመቱን ሙሉ የሥራ ዕድል በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸወን ተናግረዋል።