የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ስኬታማ ውጤቶች ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማዕከል አድርጓታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ስኬታማ ውጤቶች ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማዕከል አድርጓታል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ስኬታማ ውጤቶች ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማዕከል ተደርጋ እንድትታይ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ገለጹ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ 25ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
በስብሰባውም የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የፌዴራል መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን በተመለከተ በሚያቀርቡት የበጀት መግለጫ ላይ ይወያያል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ፤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበውን የፌዴራል መንግሥት የ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን አስመልክቶ መግለጫ አቅርበዋል።
በመግለጫቸው፤ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ክፍያ ሚዛን ጫናና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ተግዳሮቶችን በእጅጉ መቅረፍ ተችሏል ብለዋል።
የገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሽግግሩም የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ከመቅረፉ ባለፈ፣ በሕጋዊና በትይዩ (ጥቁር) ገበያ መካከል የነበረውን የተመን ክፍተት በከፍተኛ ደረጃ አጥብቦታል ብለዋል።
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት የሸቀጦች ወጪ ንግድ ገቢ በ2016 ከነበረበት 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ወደ 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ዕድገት በማስመዝገብ የ119 በመቶ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በመገባደድ ላይ በሚገኘው በዚህ በጀት ዓመትም የወጪ ንግድ ከፍተኛ አፈጻጸም በመቀጠሉ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨቱ ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ፣ ጎረቤት ሀገራትን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ በማድረግ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያውን በተመለከተም፤ ማሻሻያው የፋይናንስ ዘርፉን ውጤታማና ጤናማነት በማረጋገጥ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያሳልጥ ዘመናዊና ገበያ መር የወለድ ምጣኔ እንዲፈጠር ማድረጉን አስረድተዋል።
ይህም የንግድ ባንኮች ከደንበኞቻቸው ጋር በገበያ ሁኔታዎች ላይ በመመስረት የወለድ ተመኖችን እንዲደራደሩና እንዲወስኑ ሙሉ መብት አስገኝቶላቸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የተዘረጋውን ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ የሚያጠናክሩ በርካታ ለውጦችን በመተግበር የፋይናንስ ዘርፉን ደህንነት ለማስጠበቅና ለማዘመን እየሠራ ይገኛል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰነደ መዋለ ንዋይ (ካፒታል) ገበያ መመስረቱ ዘመናዊ የካፒታል ሥርዓትን በመዘርጋት፣መንግሥትና ኩባንያዎች የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ፍላጎታቸውን ማሰባሰብ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዝቅተኛ ገቢ ባለው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ የሚያስከትለውን የኑሮ ጫና ለመቋቋም መንግሥት ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ የማኅበራዊ ድጎማ ወጪዎችን ተግባራዊ ማድረጉን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በዚህም መሠረት በነዳጅ፣ በአፈር ማዳበሪያ፣ በልማታዊ ሴፍቲኔት፣ በምግብ ዘይት፣ በመሠረታዊ መድኃኒቶች እንዲሁም በፌዴራልና በክልል የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ላይ ከፍተኛ የበጀት ድጎማ ተደርጓል።
ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት የኢኮኖሚ ዕድገት ውጤቶች የውጭ ባለሀብቶችን ቀልብ በመሳብ ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻቸው እያደረጓት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ በተያዘው በጀት ዓመት የ10 ነጥብ 2 በመቶ ጥቅል ሀገራዊ ዕድገት (GDP) ማስመዝገብ እንደሚቻል በርካታ የኢኮኖሚ አመላካቾች ያሳያሉ ብለዋል።