ቀጥታ፡

በአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራን ከኢኮኖሚ ፍላጎት ጋር የሚያጣጥም ክህሎትና ብቃት ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራን ከኢኮኖሚ ፍላጎት ጋር የሚያጣጥም የዜጎች ክህሎትና ብቃት ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚገባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ክሌቨር ጋቴቴ ገለጹ።

በሥራ ፈጠራ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የአፍሪካ ዴቨሎፕመንት ኢምፓክት ፎረም 2026 በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) መካሄድ ጀምሯል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ክሌቨር ጋቴቴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካን መጻኢ ዕድል ለመወሰን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ኢንዱስትሪ ምኅዳር መገንባት ይገባል ብለዋል።

ከዓለም አቀፍ አኳያም አህጉሪቷ የታደለችውን ስትራቴጂክ የሰው ሃብት የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አህጉራዊ ዕድገትና ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለዚህም የአፍሪካ ሀገራት መንግሥታት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ የሥራ ፈጣሪዎች፣ የልማት ተቋማትና የግል ማኅበራት አዳዲስ መፍትሄዎችን እያፈለቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ፎረሙም የአፍሪካዊያንን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማሻሻል ተግባራዊ መፍትሄዎችን ለማራመድ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ባለሀብቶችንና የልማት አጋሮችን የሚያገናኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአህጉሪቷ ዜጎችን በሚፈለገው መጠን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ሁሉንም ያካተተ ምቹ ሥነ-ምህዳር መገንባት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለዚህም ከአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ፋላጎቶች ጋር የሚጣጣሙ የዜጎች ክህሎትና ብቃት የሚያጎለብት ኢንቨስትመንትን ማሳደግ እንዲገባ አስገንዝበዋል።

ለወጣቶችም የትምህርት ሥርዓቶችን የሚያጠናክር የዲጂታል ስልጠና በማሳደግ በነባርም ሆነ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ክህሎቶች ማስታጠቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም አዳዲስ ጀማሪ ስራዎችን (start-ups) መደገፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአፍሪካን ኢንዱስትሪ ልማት ከእሴት ሰንሰለት ጋር በማሰናሰል የአህጉሪቷ ዕድገትና ብልጽግናን ማፋጠን እንደሚያስፈል ጠቁመዋል።

አፍሪካ ጥሬ ዕቃዎችን ወደ ውጭ በመላክ እና የተጠናቀቁ ምርቶችን ወደ ውስጥ በማስገባት በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደማትችል አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም