ቀጥታ፡

በጅማ ዞን በዚህ ዓመት ከ 12 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆነዋል

ጅማ፤ ሰኔ 4/2018(ኢዜአ)፡- በጅማ ዞን በበጀት ዓመቱ  ከ 12 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጅማ ሪጅን ገለጸ።

የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ሰቦቃ፣ በበጀት ዓመቱ የዞኑ ነዋሪዎችን የመብራት ተደራሽነትን ለማስፋፋት በትኩረት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በዚህም በዞኑ ሁሉንም ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ ጥያቄ ሲነሳባቸው የነበሩ ቀበሌዎችንም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ በስፋት መሠራቱን ነው ያብራሩት።

ከዚህ በተጨማሪም በዞኑ የማሰራጫ ጣቢያዎችን ቁጥር 21 በማድረስ የመብራት መቆራረጥን ለመቅረፍ የተሠራው ሥራም ውጤታማ እየሆነ ነው ብለዋል።

ያረጁ ምሰሶዎችን የማደስ እና በኮንክሪት የመተካት ሥራ መሠራቱን የገለጹት አቶ ሲሳይ፣ በዚህ ዓመት የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ ከ50 በላይ ተጨማሪ ትራንስፎርመሮች መተከላቸውን አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ዘመናዊ ቆጣሪዎችን ለነዋሪዎች በማቅረብ አጠቃላይ አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

በዚህ ወር መጨረሻም የዘንድሮውን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ 15 ሺህ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል።

የጅማ ዞን ጎማ ወረዳ ጂማቴ ደሩ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አባነጋ ኃጂ ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው መብራት ተደራሽ ባለመሆኑ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ገልጸው ፣ለዘመናት የነበረው ጥያቄያችን አሁን ተፈቷል ብለዋል።

ሌላኛው የጅማ ከተማ በቾ ቦሬ ቀበሌ ነዋሪዎች ካሊድ ዛኪር እና መሐመድሳሊህ ሀቢብ፣ ዘንድሮ ተጨማሪ ትራንስፎርመር በመተከሉ ከዚህ ቀደም የነበረው መቆራረጥ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም