ቀጥታ፡

ጽንፈኛ ቡድኑ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዳይሳካ ያደረገው ሙከራ በሰላም ወዳዱ ሕዝብ ህልም ሆኖ ቀርቷል-አቶ ጣሂር መሀመድ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ ጽንፈኛ ቡድኑ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዳይሳካ ያደረገው ሙከራ በሰላም ወዳዱ ሕዝብ ህልም ሆኖ መቅረቱን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አባል አቶ ጣሂር መሀመድ ገለጹ።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝብ ተሳትፎ ጎልቶ የታየበት ስኬታማ ሆኖ ተጠናቋል።

ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ታዛቢዎች ምርጫው ዲሞክራሲያዊ፣ አካታችና ምሳሌነቱ የሚጠቀስ መሆኑን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አባል አቶ ጣሂር መሀመድ በምርጫውና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አቶ ጣሂር እንዳሉት፤ የአማራ ክልል ሕዝብ በነጻነት የራሱን መሪዎች እንዳይመርጥ ጽንፈኛው ቡድን ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ጭምር በመቀናጀት ምርጫውን የማደናቀፍ ተግባራት ላይ ተጠምዶ መቆየቱን አንስተዋል።

ጽንፈኛው ቡድን መራጩን ሕዝብ በዚህ ምርጫ ትሳተፍና፣ ይሄን ታደርግና የሚሉ ዛቻና ማስፈራሪያዎች ጭምር በመጠቀም አደገኛ ቅስቀሳዎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ በመሰል እንቅስቃሴዎች ሕዝቡ ዋጋ ሲከፍል መቆየቱን ጠቅሰዋል።

እንዲያም ሆኖ የአማራ ክልል ሕዝብ ጫናዎችን ተቋቁሞ ለሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ በመስጠት ምርጫውን እንዲሳካ አድርጓል ያሉት አቶ ጣሂር፤ ለዚህ በሳል ውሳኔ ሕዝቡ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።

በዚህ ሁሉ ጫና ውስጥ ሕዝቡ ወጥቼ እመርጣለሁ፤ የምፈልገው መደበኛ የሆነ የመንግሥት አስተዳደር ነው በሚል መርህ በመመራት ምርጫውን ማሳካቱ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም በተጻጻሪው የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን የአማራን ሕዝብ እንደማይገልጸው ማሳያ መሆኑንም አስረድተዋል።

በሕዝቡ ድምጽ የሚመሰረተው መንግሥት ዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ በከፍተኛ ኃላፊነት ሊሰራ እንደሚገባ ያመላከተ ነው ያሉት አቶ ጣሂር፤ ሕዝቡ በሰላም ዙሪያ በሚሰሩ ሥራዎች ተባባሪና ቁርጠኛ መሆኑን ያሳየበት ምርጫ መሆኑንም አብራርተዋል።

በአማራ ክልል የተካሄደው ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይልና ሚሊሻዎች በየደረጃው ካሉ አመራር ጋር በቅንጅት ያከናወኑት ተግባር ጉልህ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።

ይሄ ውጤት ደግሞ በመንግሥት እና በመደበኛ ሥርዓት ሕዝቡ እንዲተማመን ያስቻለ ነው ብለዋል።

እንደ አቶ ጣሂር ገለጻ፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጋፋ የኃይል አሰላለፍ ሕዝብንም ሀገርንም ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ሕዝቡ በዚህ ላይ ግንዛቤ ጨብጦ ለሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ እየሰራ ነው።

"ጥያቄዎች የሚመለሱት በኃይል ነው" የሚል አቋም ይዘው እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላት ሰላማዊ መንገድን በመምረጥ ችግሮች በውይይት የሚፈቱበት አውድ መፍጠር ላይ ሊሰሩ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

መንግሥት የሰላም ጥሪ አቅርቦ በሩን ክፍት ማድረጉ የሚበረታታ መሆኑን አመልክተው፤ ይሄ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም