ቀጥታ፡

የነዋሪዎችን መረጃ በዘመናዊ መንገድ የማደራጀት ሥራ ለአገልግሎት አሰጣጥ መሳለጥና ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት መረጃዎችን በዘመናዊ መንገድ ለማደራጀት እየተከናወነ ያለው ሥራ የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ ከማድረግ ባለፈ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለፁ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የነዋሪዎችን መረጃ በዘመናዊ መንገድ ለማደራጀት እየተከናወነ ያለውን ተግባር ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ እንደሀገር የዲጂታላይዜሽን ሥራ  በተግባር የሚታይበት ደረጃ ደርሷል።

በተለይም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተሰሩ ስኬታማ ሥራዎች አይተኬ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም እነዚህ ስኬታማ ሥራዎች ይበልጥ ለማጠናከር መረጃን የሚያሰባስቡ ማናቸውም የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አሰራራቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ማሻገር አለባቸው ብለዋል።

በተለይም በሲቪል ምዝገባ ረገድ ከውልደት እስከ ሞት ያሉ ማንኛቸውም የነዋሪዎችን መረጃዎችና ሰነዶች ከባህላዊ የወረቀት አያያዝ ወጥተው በዲጂታል መንገድ መያዝ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ይህም ተቋማዊ አሰራርን በማዘመን ረገድ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ የመረጃዎች ዲጂታል መሆን ቢሮክራሲን በማስቀረት ፍጹም ግልፀኝነትን ያረጋገጠ አሰራር ለመዘርጋት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የያዘችውን የዲጂታል 2030 ራዕይ ስኬታማ ለማድረግ የበኩሉን ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አመላክተዋል።

በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የጀመረው የሰነድ አስተዳደር ሥርዓት  በሁሉም የመንግሥት ተቋማት ዘንድ ተሞክሮው ሊሰፋ የሚገባው ነው ብለዋል።

ይህም ዜጎች በቀላሉ መረጃዎችን ማግኘት የሚችሉበትን የኦንላይን አገልግሎት ሥርዓት ለመዘርጋት እንደ ማሳያ የሚወሰድ ተግባር መሆኑም አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ንጉሴ በበኩላቸው፤ ህዝቡ በቤቱ ሆኖ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችለውን አዲስ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ሰፊ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ብለዋል። 


 

ይህም ለዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጥ መሰረት እንደሆነ ተናግረው፤ተገልጋዩ አገልግሎቱን በኦንላይን ይጠይቃል፣ እኛም በቀጥታ የምንሰጥበትን ቀልጣፋ ሂደት ይፈጥራል ብለዋል።

አሰራሩ ተግባራዊ መደረጉ የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን እንግልትን ሙሉ በሙሉ እንደሚያስቀር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም