በዞኑ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የዓሳ ዕርባታ ስራ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነትን እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የዓሳ ዕርባታ ስራ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነትን እያሳደገ ነው
ደብረ ብርሃን ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፡- በሰሜን ሸዋ ዞን በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የዓሳ ዕርባታ ስራ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነትን እያሳደገ መሆኑ ተገለጸ።
በዞኑ በዓሳ ልማቱም 1 ሺህ 374 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኝም ተገልጿል።
በዞኑ እንስሳትና ዓሳ ሀብት መምሪያ የዓሳ ልማት አስተዳደር ባለሙያ ወይዘሮ እማዋይሽ የኋላ እሸት እንዳሉት የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በዓሳ ልማት ዘርፍ ምርታማነትን እና የተሳታፊዎችን ቁጥር እያሳደገ ነው።
በመርሃ ግብሩ ወጣቶች፣ ሴቶችን እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በወንዞች ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረን የዓሳ እርባታ ስራ በመርሃ ግብሩ በአርሶ አደሮች ጓሮ በተዘጋጁ ኩሬዎች እንዲከናወን በመደረጉ የዓሳ ምርታማነት ጨምሯል ብለዋል።
በዚህም የዓሳ ዕርባታ ስራው በኩሬዎችና በወንዞች ላይ በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህም ራስን በምግብ ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ከመደገፍ ባለፈ ዓሳን በመመገብ ነፍሰ ጡር እናቶችና ህፃናት ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ ማስቻሉንም አክለዋል።
አርሶ አደሩ ዓሳን ለቤት ውስጥ ፍጆታው ከመጠቀም ባሻገር ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እያሳደገ መምጣቱን ገልፀዋል።
በዓሳ ልማቱም 1 ሺህ 374 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኝ ገልጸው እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም 26 ሺህ 364 የዓሳ ጫጩቶች በኩሬዎች እንዲራቡ በመደረግ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።
በባሶና ወራና ወረዳ የዲቡት ቀበሌ አርሶ አደር ታደሰ ማሞ እንዳሉት የዓሳ ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ስርዓተ ምግብን ከማሻሻል ባሻገር ተጨማሪ ገቢ እንድናገኝ አስችሎናል።
በቀጣይ ከወረዳው አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ተጨማሪ የዓሳ ጫጩቶችን በማምጣት የተሻለ ምርት ለማምረት ማቀዳቸውንም አክለዋል።