ቀጥታ፡

የትምህርት ሥርዓትን ከገበያ ፍላጎት ጋር ማጣጣም ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦የትምህርት ሥርዓትን ከገበያ ፍላጎት ጋር ማጣጣም ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሀፊ አሚና መሐመድ ገለጹ።

በሥራ ፈጠራ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የአፍሪካ ዴቨሎፕመንት ኢምፓክት ፎረም 2026 በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) መካሄድ ጀምሯል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሀፊ አሚና መሐመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አፍሪካ ታላላቅ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች ባሉበት ወሳኝ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡


 

በዚህ ወቅት ጥራትና ዘላቂነት ያላቸው የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓቶችን ከገበያው ትክክለኛ ፍላጎት ጋር ማጣጣም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይም በፍጥነት እያደገ የመጣውን የአፍሪካ ወጣት ቁጥር ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጥራት ያላቸው የሥራ ዕድሎችን መፍጠር አፋጣኝ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ባለፉት ዓመታት ከአምራች ኢንዱስትሪ መስፋፋት እስከ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና የክህሎት ልማት ያሉ የአፍሪካን አንገብጋቢ ተግዳሮቶች ለመፍታት ከመንግሥታት፣ ከቀጣናዊ ተቋማትና ከግል ዘርፉ ጋር በጋራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ከዚህ የጋራ ሥራም ትልቅ ትምህርት መገኘቱን ጠቅሰው፣ምርምር፣መረጃና ማስረጃዎች ብቻቸውን ለውጥ አያመጡም፤ ከንግግርና ከሪፖርት ባለፈም ወደ ተግባራዊ እርምጃ መግባት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል።

የስራ ዕድሎችን መፍጠር በመንግሥታት ብቻ ሊሳካ እንደማይችል ጠቁመው፤ይህም የፖሊሲ አውጪዎችን፣ ተመራማሪዎችን፣ የልማት አጋሮችንና የግል ዘርፉን በአንድ ላይ የሚያገናኝ ንቁ ሥነ-ምሕዳርን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

የዘንድሮው ፎረም መፍትሔዎችን ለመለየት፣ጠንካራ አጋርነትን ለመገንባትና ተግባራዊ የመድረሻ መንገዶችን ለመንደፍ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በአንድ ላይ ያገናኘ ሲሆን፣ከውይይት ባለፈ በመላው አፍሪካ ላሉ ወጣቶች ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀይሩ ትርጉም ያላቸው ተግባራት እንደሚጠበቁበት ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም