በዞኑ በመኸር እርሻ ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ግብ ተይዞ የማሳ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በመኸር እርሻ ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ግብ ተይዞ የማሳ ዝግጅት እየተደረገ ነው
ጊምቢ፤ ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ):-በምዕራብ ወለጋ ዞን በዘንድሮ የመኸር እርሻ ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ግብ ተይዞ የማሳ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈይሳ ሀምቢሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2018/19 የመኸር ወቅት ከ484 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ነው።
ዕቅዱን ለማሳካትም የተቀናጀ የግብርና ሥራ መጀመሩን ገልጸው፣ እስካሁን በተደረገ ጥረት 155 ሺህ 322 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን መቻሉን ተናግረዋል።
ቀሪውን መሬት በተደጋጋሚ በማረስ ለዘር እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፣ በምርት ዘመኑ ለሜካናይዜሽን እርሻም ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
ውጤታማ የግብርና ሥራ ለማከናወንም በዞኑ 28 የእርሻ ትራክተሮች ሥራ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለልማቱ እስካሁን ድረስ 116 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የአፈር ማዳበሪያ የተሰራጨ ሲሆን ከዚህ በተጓዳኝ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት አዘጋጅቶ እንዲጠቀም እየተደረገ መሆኑን አቶ ፈይሳ ተናግረዋል።
የመኸር እርሻን ውጤታማ ለማድረግም ለማልማት ከታቀደው መሬት ውስጥ አብዛኛው መሬት በኩታ ገጠም አሰራር እንዲለማ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ በልማቱ እየተሳተፉ ካሉ የበጊ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ዳዊት ታሲሳ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፈው ዓመት የመኸር እርሻ ከአንድ ሄክታር መሬት 26 ኩንታል የበቆሎ ምርት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።
ዘንድሮ ከሄክታር እስከ 34 ኩንታል የበቆሎ ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን ገልጸው ለእዚህም ማሳቸውን ደጋግመው በማረስና በማለስለስ በዘር እየሸፈኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ውጤታማ ልማት እንዲያከናውኑ የአፈር ማዳበሪያ በጊዜ ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ የእዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ከማል ቦካ ናቸው።
ያዘጋጁትን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በእርሻ ማሳቸው ላይ በመበተንና በማዋሃድ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ተግተው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ባላቸው አንድ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ በቆሎና ስንዴ በማልማት ከ32 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆኑንም አመልክተዋል።
የበጊ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወቅጋሪ ከበደ በበኩላቸው፣ በወረዳው በዘንድሮው የመኽር ወቅት 44 ሺህ 930 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች እንደሚለማ ተናግረዋል።
የአርሶ አደሩ የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እየተሻሻለ በመምጣቱ በዘንድሮው የመኸር አዝመራ አብዛኛው መሬት በኩታ ገጠም ለማልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለመኸር እርሻው የሰብል ልማት ስራው እስካሁን ድረስ 4ሺህ 389 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱንም አስታውቀዋል።