ቀጥታ፡

በክልሉ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡና ገበያን የሚያረጋጉ የግብርና ልማት ስራዎች ይጠናከራሉ

ሃዋሳ፤ ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ) ፡-በሲዳማ ክልል በክልሉ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡና ገበያን የሚያረጋጉ የግብርና ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

የሲዳማ ክልል አቀፍ የመኸር እርሻ ንቅናቄ መድረክ በሃዋሳ እየተካሄደ ነው።


 

የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡና ገበያን የሚያረጋጉ የግብርና ልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

ለዚህም ባለፉት ዓመታት ጦሙን የሚያድር መሬት እንዳይኖር የጋራ መግባባት ተፈጥሮ በተሰራው ስራ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸው በተያዘው የምርት ዘመንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የግብርና ምርታማነቱን ለማሳካትም ከበልግ ምርቱ መሰብሰብ ጎን ለጎን የመኸር ሰብልን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በዚህም የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ትርፍ አምርቶ ገበያን ለማረጋጋትና የኑሮ ውድነትቱን ተፅዕኖ ለመቀነስ ለሚያስችሉ የግብርና ልማት ስራዎች ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በምርት ዘመኑ የተያዘውን እቅድ ለማሳካትም በየደረጃው ያለ አመራር የህብረተሰቡን አቅም በማስተባበር ለውጤቱ በትጋት መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።


 

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው በዘንድሮው መኸር ከ169 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ይለማል ብለዋል።

በዚህም ከ16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቅሰው ለዚህም በየደረጃው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የዛሬው መድረክ አላማም አመራሩ በእቅዱ ላይ የጋራ መግባባት ፈጥሮ ወደ ተግባር እንዲገባ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በመድረኩ ለመኸር ወቅት የተዘጋጀ ዝርዝር እቅድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም