የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ከ2 ነጥብ 339 ትሪሊየን ብር በላይ ሆኖ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ከ2 ነጥብ 339 ትሪሊየን ብር በላይ ሆኖ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦የፌዴራል መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ከ2 ነጥብ 339 ትሪሊየን ብር በላይ ሆኖ ቀርቧል።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ 25ኛ መደበኛ ስብሰባውን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የፌዴራል መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን በተመለከተ በሚያቀርቡት የበጀት መግለጫ ላይ እየተወያየ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ በመግለጫቸው፤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበውን የፌዴራል መንግሥት የ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን አስመልክቶ መግለጫ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዞና በመገባደድ ላይ ያለውን በጀት ዓመት የኢኮኖሚ ዕይታና አፈፃጸም በማመላከት ተደግፎ የቀረበውን የቀጣይ በጀት ዓመት የበጀት ድልድል የተመሰረተባቸውን ታሳቢዎች በዝርዝር አቅርበዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የረቂቅ በጀቱን መግለጫ ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፥ በጀቱ መንግሥት የያዛቸውን የልማትና የማክሮ ኢኮኖሚ ዕቅዶች ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ነው።
ለ2019 በጀት ዓመት ከቀረበው በጀት ውስጥ 1 ነጥብ 236 ትሪሊየን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 568 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለካፒታል ወጪ እንደሚውል አስረድተዋል።
በተጨማሪም 520 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት የበጀት ድጋፍ እንዲሁም 14 ቢሊየን ብር ለክልሎች የዘላቂ ልማት ግብ ማስፈጸሚያ ይውላል ነው ያሉት።
ከአጠቃላይ በጀቱ ውስጥ 52 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆነው ከፍተኛ በጀት ለመደበኛ ወጪ የተመደበ መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህም ውስጥ 542 ቢሊየን ብር ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ የእዳ ክፍያ እንደሚውል ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ከዚሁ የመደበኛ ወጪ ውስጥ 236 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለማዳበሪያ፣ ለነዳጅ ድጎማ እንዲሁም የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅትን ካፒታል ለማሳደግ የተመደበ ነው ብለዋል።
ለመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ለደመወዝ፣ ለአበልና ልዩ ልዩ ክፍያዎች 170 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር መመደቡን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2019 በጀት ዓመት 10 ነጥብ 1 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል ነው ያሉት።
የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የ2019 በጀት የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት የሚያሳድረውን ተጽእኖ ከግምት በማስገባት መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
በ2019 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት ጠቅላላ ገቢ 1 ነጥብ 817 ትሪሊየን ብር እንደሚሆን ግምት ተወስዷል ብለዋል።
ከዚህም ውስጥም 1 ነጥብ 6 ትሪሊየን ብር ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች እንደሚሰበሰብ መታቀዱን አመልክተዋል።
ለ2019 በጀት ዓመት የቀረበው 2 ነጥብ 339 ትሪሊየን ብር በጀት ከዘንድሮው በጀት ዓመት አንጻር የ21 ነጥብ 3 በመቶ እድገት እንዳለው ተናግረዋል።