ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ አዲሱ የተሽከርካሪ ሠሌዳ መሰጠት ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ አዲሱ የተሽከርካሪ ሠሌዳ መሰጠት መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዘገየ በላይነህ በሰጡት መግለጫ፤ አዲሱ የተሽከርካሪ ሠሌዳ ከዛሬ ጀምሮ መሰጠት መጀመሩን ይፋ አድርገዋል፡፡

አዲሱ የተሽከርካሪ ሠሌዳ ሀገራዊ ይዘትን የተላበሰ፣ ተመሳስሎ መሠራት እንዳይቻል ሆኖ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ባለሥልጣኑ አገልግሎቱን ለማዘመንና ቁጥጥሩን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ለዚህም አዲሱን የተሽከርካሪ ሠሌዳ አጠቃላይ ይዘትና አተገባበር ከበፊቱ በተሻለ መልኩ ሥራዎችን ለማዘመን፣እንዲሁም ኢትዮጵያን የሚገልጹ መለያዎችን የያዘ እና ዓለም አቀፍ መስፈርቱን የተከተለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አዲሱ ሠሌዳ ከዚህ በፊት በሌላ መልኩ ማኅበራዊ መስተጋብርን በማጠናከር እና የሀብት ብክነትን የመከላከል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ መኖሩን ገልጸዋል።

አዲሱ ሠሌዳ ከዛሬ ቀን ጀምሮ መሰጠት እንደሚጀምር ጠቅሰው፣ሠሌዳው የተለያዩ መረጃዎችን የሚይዝ በመሆኑ ለሕግ ማስከበር ሥራ የሚመች፣ ቶሎ የማይበላሽ እና ወጪ ቆጣቢ መሆኑን አብራርተዋል።

ሠሌዳው ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ መሰጠት መጀመሩን እና ተገልጋዮች በተመዘገቡበት ቅደም-ተከተል እንደሚወስዱ፤በክልል ከተሞች ደግሞ በቅርቡ እንደሚጀምር ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም