ቀጥታ፡

ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሰለፍ በብሄራዊ ጥቅሟ ላይ ክህደት የሚፈፅሙ ባንዳዎችን መታገል ሀገራዊ ግዴታችን ነው-የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

ደሴ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፡-ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሰለፍ በብሄራዊ ጥቅሟና ክብሯ ላይ ክህደት የሚፈፅሙ ባንዳዎችን መታገል ሀገራዊ ግዴታችን ነው ሲሉ የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር በትብብር በመስራት ብሄራዊ ጥቅሟን የማስከበርና ህልውናዋን የማስጠበቅ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን አጠናክራ ቀጥላለች።

የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄዋ ምላሽ እንዲያገኝ በታሪክ፣ በመልክአ ምድር እንዲሁም በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት እየሰራች መሆኑ ይታወቃል።

በመሆኑም የባህር በር ጥያቄና ሌሎችም የሀገር ብሄራዊ ጥቅሞች የትውልዱ ጉዳይ ሆነው ተጠናክረው የቀጠሉ አጀንዳዎች ናቸው።

ይሁን እንጂ የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም፣ክብርና ሉአላዊነት በመፃረር ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር በባንዳነት የተሰለፉ መኖራቸው የሚታይ እውነታ ሆኗል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የተለያዩ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሰለፍ በብሄራዊ ጥቅሟና ክብሯ ላይ ክህደት የሚፈፅሙ ባንዳዎችን መታገል ሀገራዊ ግደታችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) የደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከድር ይመር፤ የሀገር ሰላም፣ ሉዓላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ ለማንም ቢሆን ለድርድር የማይቀርብ የሀገር ህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ከዚህ በተቃራኒ ከጠላት ጋር የሚቆም የፖለቲካ ፓርቲ፣ ግለሰብም ሆነ ሌላ አካል ካለ የሀገሩን ጥቅም አሳልፎ እየሰጠ ስለመሆኑ ግልጽ መሆኑን አንስተዋል።

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ልማት፣ ብሄራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት መከበር ፓርቲያቸው የጸና አቋም ያለው መሆኑን አንስተው፥ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እንሰራለን ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የደቡብ ወሎና ደሴ ከተማ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሻምበል ደምሌ ተረፈ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሃሳብ ልዩነት ቢኖረንም በሀገር ሉአላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ ላይ ልዩነት የለንም ብለዋል።

በመሆኑም ለኢትዮጵያ ሰላም፣ልማትና ለብሄራዊ ጥቅሟ መከበር የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አያሌው አሸብር፤ፓርቲያችን በሀገር ሉአላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ ጠንካራ አቋም ይዞ እየሰራ ይገኛል፤ በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ላይ የውስጥና የውጪ ጠላቶች የሚያደርጉትን ማናቸውም የጥፋት እንቅስቃሴ የማንቀበለውና የምንታገለው ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም