መንግስታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ህዝቡ በመቅረቡ የመሰረተ ልማት ችግሮች በህዝብ ተሳትፎ ለመፍታት እያስቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ህዝቡ በመቅረቡ የመሰረተ ልማት ችግሮች በህዝብ ተሳትፎ ለመፍታት እያስቻለ ነው
ሮቤ፣ ሰኔ 4 /2018 (ኢዜአ):- በባሌ ዞን መንግስታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ወደ ህዝቡ በመቅረቡ የመሰረተ ልማት ችግሮች በህዝብ ተሳትፎ ለመፍታት እያስቻለ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት አዲስ የቀበሌ አደረጃጀት ተዘርግቶ ህዝቡ መንግስታዊ አገልግሎቶችን በቅርበት እያገኘ መሆኑ ይታወቃል።
በባሌ ዞን የተዘረጋው የቀበሌ አደረጃጀትም የህዝብን የልማት ተሳትፎ በማሳደግ የመሰረተ ልማት ችግሮች በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲፈቱ ዕድል መፍጠሩን የዞኑ አስተዳደር ገልጿል።
በብልጽግና ፓርቲ የዞኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አፍራሳ እንደገለጹት፤ የቀበሌ አደረጃጀቱ የህብረተሰቡን የልማት ተሳትፎ በማሳደግ የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዲፈቱ ዕድል እየፈጠረ ነው።
ይህ አደረጃጀት የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎትና የልማት ጥያቄዎችን በቅርበት ለመመለስ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑንም አክለዋል።
ከዚህ በፊት ህብረተሰቡ ከፍትህና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስጨረስ ወደ ወረዳና ዞን ማዕከላት በመመላለስ ለአላስፈላጊ ወጪና ለስራ ጊዜ መባከን ይዳረግ ነበር ያሉት ኃላፊው፤ በአዲሱ አደረጃጀት እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ከማግኘታቸውም በላይ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለማፋጠን ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።
በዚህም በህዝብ ተሳትፎ እንዲሁም በመንግስት አቅም የቀበሌ ጽሕፈት ቤቶች ግንባታን ጨምሮ የትምህርት ቤቶች፣ የመንገድና የድልድይ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑን በአብነት አንስተዋል።
የሀረና ቡሉቅ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሀሰን በበኩላቸው፤ አዲሱ አደረጃጀት የወረዳውን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በቅርበት ለመመለስ እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህዝቡ ተሳትፎ የተሰሩ የድልድይ፣ የመንገድ፣ ሼዶችና የቀበሌ ጽህፈት ቤቶች ግንባታ ሥራዎችም የአደረጃጀቱ ውጤቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የወረዳው ነዋሪዎች መካከል አቶ በከር ሱልጣን፤ የቀበሌ አደረጃጀቱ የአካባቢውን ህብረተሰብ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች በቅርበት እንዲመለሱ እያገዘ መሆኑን ገልጸው፣ በህዝብ ተሳትፎ የተገነቡትን ድልድይና የወጣቶች መስሪያ ሼድ በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
ሌላው የወረዳው ነዋሪ አቶ አህመድ መሐመድ በበኩላቸው፤ የቀበሌ አደረጃጀቱ በአካባቢያቸው ተግባራዊ መደረጉ ከዚህ በፊት መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት ያስቀረና በልማት ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።
በባሌ ዞን በአጠቃላይ 189 አዲስ የተደራጁ ቀበሌዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በእነዚህ ቀበሌዎች የተሟላ የሰው ኃይል ተመድቦ ለማህበረሰቡ በቅርበት አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ታውቋል።