ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን አረጋገጡ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን አረጋገጡ
አዲስ አበባ፤ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ትስስራቸውን ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ቢያንካ ኦዱሜግዉ-ኦጁክዉ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ውይይት አድርገዋል።
ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ እ.አ.አ ከ1960ዎቹ አንስቶ የዘለቀ የረጅም ጊዜ ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።
ይህንን የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርም በጋራ ጥቅሞች ላይ ያተኮረ ቀጣይነት ያለው ቅንጅትና ምክክር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የናይጄሪያዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ቢያንካ ኦዱሜግዉ-ኦጁክዉ በበኩላቸው፥ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
ናይጄሪያ በተለያዩ የልማትና የፖለቲካ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ይበልጥ በቅርበት ለመስራት ያላትን ዝግጁነትም አምባሳደር ቢያንካ አረጋግጠዋል።
በዚሁ የሁለትዮሽ ምክክር ላይ የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርያሥላሴ እና የናይጄሪያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ እና የፍትህ ሚኒስትር ላቲፍ ኦላሱንካንሚ ፋግቤሚ የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ሚኒስትሮቹ የተፈራረሙት ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል የፍርደኞች ልውውጥ ወይም ማስተላለፍን (Transfer of Sentenced Persons) የተመለከተ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ የፍትህ ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ ለቀጣይ ትብብሮች መሰረት የሚጥል የሕግ ማዕቀፍ እንደሚፈጥር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሁለቱ ወገኖች ውይይት እና ስምምነት በኢትዮጵያና በናይጄሪያ መካከል ያለውን አጋርነት ይበልጥ እንደሚያሳድገውም ገልጿል።