አበረታች ቅመሞች የመጠቀም ወንጀልን ለመከላከል የፍትህ አካላት ቅንጅታዊ አስተዋጾ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አበረታች ቅመሞች የመጠቀም ወንጀልን ለመከላከል የፍትህ አካላት ቅንጅታዊ አስተዋጾ ወሳኝ ነው
አዳማ፤ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፦ አበረታች ቅመሞች የመጠቀም ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት የፍትህ አካላት አስተዋጾ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከፍትህ አካላት ጋር ወንጀሉን በቅንጅት የመከላከል ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ አካሂዷል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል በወቅቱ እንደገለጹት፤ የተቀናጀ የፀረ-አበረታች ቅመሞች መከላከልና መቆጣጠር ሥራ የዜጎችን ሁለንተናዊ ደህንነት ለመጠበቅ የሚደረገው ጥረት አንዱ አካል ነው።
አበረታች ቅመሞችን መጠቀም በህግ የተከለከለ የወንጀል ተግባር በመሆኑ፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የፍትህ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
የውይይት መድረኩም የፀጥታና የፍትህ አካላት ከባለስልጣኑ ጋር በቅንጅትና በትብብር እንዲሰሩ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
"ድርጊቱ የአትሌቲክስ ዘርፉን ከመጉዳት ባለፈ በሀገር ገፅታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራት አስፈልጓል" ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የህግ ማዕቀፎችን ከማውጣትና የባለድርሻ አካላትን ትብብር ከማጠናከር አንጻር አመርቂ ሥራዎች እንደተሰሩ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህን ለማስቀጠል ቅንጅታዊ ሥራን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ድርጊቱ በስፖርተኞች ላይ የስነ-ልቦና ጫና ከመፍጠር ባለፈ የተወዳዳሪነት አቅምን የሚፈታተን ወንጀል በመሆኑ መከላከሉና መቆጣጠሩ የጋራ ሃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የባለስልጣኑ የውጤት አስተዳደርና ህግ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ንጋቱ መኮንን እንዳሉት፤ አበረታች ቅመሞችን የመጠቀም የህግ ጥሰቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል።
እስካሁን እየተወሰዱ ያሉ የህግ እርምጃዎች በሚፈለገው ደረጃ ባለመሆናቸው ችግሩን ከመፍታት አኳያ ክፍተቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ችግሩን ለመፍታት የፀረ-አበረታች ቅመሞች ህግ ማዕቀፎች በተግባር ላይ ውለው ውጤታማ እንዲሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተቀናጀ መልኩ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።