ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤና የቴክኖሎጂ ውድድር ከፊታችን አርብ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፡-ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤና የቴክኖሎጂ ውድድር ከመጪው አርብ ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ 

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያካሂደውን ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤ እና የቴክኖሎጂ ውድድር በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። 


 

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ሙሉጌታ (ዶ/ር) በመግለጫቸው፤ ኢንስቲትዩቱ በምርምርና በቴክኖሎጂ ልማት ረገድ በርካታ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ይህ ዓለም አቀፋዊ የምርምር ጉባዔ እና የቴክኖሎጂ ውድድርም፤ ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ የጀመራቸውን የፈጠራና የምርምር ስራዎች ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን ይህንን ጉባኤ በስኬት ለማካሄድ ተቋሙ በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ዓለም አቀፋዊ የምርምር ጉባዔ እና የቴክኖሎጂ ውድድርም ከሰኔ 5 እስከ 7 2018 ዓ.ም የሚቆይ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡ 

በጉባኤው ከ 16 አገራት የተወጣጡ ተመራማሪዎች እና ሌሎች አካላት የሚሳተፉ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም