አመራሩ ወቅቱን የዋጀ ዕውቀትን በመታጠቅ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
አመራሩ ወቅቱን የዋጀ ዕውቀትን በመታጠቅ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅበታል
ደሴ፤ ሰኔ 3/2018(ኢዜአ)፡-አመራሩ ወቅቱን የዋጀ ዕውቀትን በመታጠቅና እንደ አስቻይ ሁኔታው በመምራት መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚገባ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ አመለከቱ።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ አካዳሚክ ስታፍ ሰራተኞችና ለካውንስል አባላት ስልጠና እየሰጡ ነው።
አቶ ዛዲግ በስልጠናው ላይ እንዳሉት፤ አመራሩ ወቅቱን የዋጀ ዕውቀትን በመታጠቅ መሰረታዊ ለውጥ ማስመዝገብ ይጠበቅበታል ብለዋል።
በተለመደውና ከዚህ ቀደም በነበሩ አሰራሮች መቀጠል ወቅቱ እንደማይፈቅድ ያስገነዘቡት አቶ ዛዲግ ከዘመኑ ጋር እኩል በመራመድና በመስራት በየዘርፉ ለውጥ ማምጣት አስፈላጊ ነው ያሉት።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አመራሩ የዓለምን ተለዋዋጭ ባህሪና ሁኔታ ተረድቶ በመምራት ውጤታማ መሆን እንዲችል ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በዚህም ለተከታታይ ሁለት ቀናት ለአመራሩ፣ ለአካዳሚክ ስታፍ ሰራተኛውና ለካውንስል አባላት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው በዚህም አቅምን በማጎልበት ውጤታማ ተግባር ማከናወን ይገባል ብለዋል።
እንዲሁም አውቆና ወቅቱን ተረድቶ በመስራት ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል ከመፍጠር ባለፈ አቅላይ የፈጠራ ስራዎችን ማብዛት እንደሚገባም አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በተግባር ተኮር ትምህርት ብቁ ትውልድ ከመፍጠር ባለፈ ቴክኖሎጂ ላይ አተኩሮ በመስራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።
ወቅቱን በዋጀ ክህሎትና እውቀት ተመርተን ውጤታማ ተግባር ለማስመዝገብ ስልጠናው ያግዘናል ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የዓለም አቀፍ ግንኘነትና አጋርነት ትብብር ዳይሬክተር አስረሴ ሞላ (ዶ/ር) ናቸው።
ስልጠናውን በንቃት በመከታተል መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
ለተከታታይ ሁለት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ላይም አመራሮች፣ የአካዳሚክ ስታፍ ሰራተኞች፣ የካውንስል አባላትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።