ቀጥታ፡

የዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የአጀንዳ ቀረፃ ዝግጅት መጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሷል - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋናው ሀገራዊ ጉባኤ የአጀንዳ ቀረፃ ዝግጅት መጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አስታወቁ።

የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር ሂደት ስኬት በዜጎች መካከል ብሔራዊ መግባባትን ማስፈን የሚያስችል ተምሳሌታዊ አቅምና ተቋም መፈጠሩን እንደሚያሳይም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሀገር አቀፍና የክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ቀረጻ ግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መርሃ ግብር እያካሄደ ይገኛል።


 

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ ያከናወናቸውን ተግባራትና የእስካሁን ሂደቶችን በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብ፣ የተሳታፊ ልየታና ዋናውን የምክክር ጉባኤ የማካሄድ ዝግጅት ስኬታማ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያንና ባለድርሻ አካላት በእስካሁኑ ሂደት የነበራቸው ንቁ ተሳትፎም ነጻና ገለልተኛ ሀገራዊ ምክክርን ማስተባበር የሚያስችል አቅምና ተቋም መፈጠሩን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውም በታላላቅ ህዝባዊ መድረኮች በቀጥታና በጥናት ለኮሚሽኑ ቀርበው የማሰባሰብ ሥራ በስፋት መከናወኑን አብራርተዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የነበረው የህዝብና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎም ለሚሰሩ ሥራዎች ጥልቅ መነሻ የሚሆኑ የሀገር ሃብቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዋናው ሀገራዊ ጉባኤ የአጀንዳ ሃሳብ የሚሰጡና የሚሳተፉ ተወካዮች በሁሉም ወረዳዎችና ከተሞች የማስመረጥ ስራ 93 በመቶ መፈጸም እንደተቻለ አስገንዝበዋል።

የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ አካታችነት፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎም ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ወሳኝ ምዕራፍ መሰረት መጣሉን አንስተዋል።

የዋናው ሀገራዊ ጉባኤ የአጀንዳ ቀረጻ ዝግጅት የማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የእስካሁኑ ሂደት ጉልህ ተሳትፏቸውን እንዲያስቀጥሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የእስካሁኑ ሂደት አካታች፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊነትም ተምሳሌታዊ የምክክር አቅምና ተቋም መፈጠሩን እንደሚያሳይ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም