ቀጥታ፡

በሆስፒታሉ ባገኘነው ነጻ የዓይን ቀዶ ሕክምና ብርሃናችን ተመልሷል

ደብረ ብርሃን፣ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፡-በደብረ ብርሃን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባገኙት ነጻ የዓይን ቀዶ ሕክምና ብርሃናቸው መመለሱን ታካሚዎች ተናገሩ።

ሆስፒታሉ ከ1ሺህ 600 ለሚበልጡ ወገኖች ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና አገልግሎት በዘመቻ እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል።


 

ከሕክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል ከመንዝ ላሎ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ አልማዝ ወርቁ ከአንድ ዓመት በላይ  የዓይን ብርሃናቸውን አጥተው ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተዳርገው ቆይተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ ባገኙት ነጻ የዓይን ቀዶ ሕክምና የዓይን ብርሃናቸውን በመመለሱ ችግራቸው መፈታቱን ተናግረዋል። 

በዓይን ሞራ ግርዶሽ ከሦስት ዓመት በላይ ለማየት ተቸግረው እንደነበረና ባገኙት ነፃ የዓይን ቀዶ ሕክምና መፍትሄ ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ነዋሪ አቶ ደበበ አበበ ናቸው። 

በዘመቻው የተደረገላቸው የዓይን ቀዶ ሕክምና ለአራት ዓመታት ከገጠማቸው የማየት ችግር እንደታደጋቸው የተናገሩት አቶ አበራ ላቀው የተባሉ ነዋሪ ደግሞ፣ በአሁኑ ወቅት የዓይን ብርሃናቸው በመመለሱ መደሰታቸውን ገልፀዋል።

የዓይን ብርሃናቸውን ባጡበት ወቅት በሰዎች ድጋፍ ይንቀሳቀሱ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህም በማህበራዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ መቆየቱን ተናግረዋል። 

የሆስፒታሉ የዓይን ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ዓለማየሁ ባየ እንዳሉት፤ የዓይን ሞራ ግርዶሽ በወቅቱ መታከም ካልተቻለ ለዓይነስውርነት የሚዳርግ በሽታ ነው። 


 

የደብረ ብርሃን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ በግል ከፍለው መታከም ለማይችሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ እና ተዛማጅ የሕክምና አገልግሎቶችን በነጻ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። 

ከሰኔ 2 እስከ 7 ቀን 2018 ዓ.ም በሚቆየው የሕክምና አገልግሎት ከ1 ሺህ 600 በላይ ሰዎችን ለማከም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ እስካሁንም ለ231 ሰዎች የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ተችሏል ብለዋል።


 

ነጻ የሕክምና አገልግሎቱ በትብብር እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው፣ ሆስፒታሉ ባለፈው ህዳር ወርም 2018 ዓ.ም ከ2 ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች መሰል የሕክምና አገልግሎት መሰጠቱን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም