በክልሉ ከብክለት የፀዳ ከባቢን በመፍጠር ጤናማና አምራች ዜጋን ለማፍራት እየተደረገ ያለው ጥረት ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከብክለት የፀዳ ከባቢን በመፍጠር ጤናማና አምራች ዜጋን ለማፍራት እየተደረገ ያለው ጥረት ይጠናከራል
ሆሳዕና ፤ ሰኔ 3/2018(ኢዜአ) ፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከብክለት የፀዳ ከባቢን በመፍጠር ጤናማና አምራች ዜጋን ለማፍራት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ ገለፀ።
ቢሮው "ብክለትን እንቀንስ፣ እንከላከል" በሚል መሪ ሐሳብ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በህግ ተከባሪነት ዙሪያ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አብርሃም መጫ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ ከብክለት የፀዳ ከባቢን በመፍጠር ጤናማና አምራች ዜጋን ለማፍራት እየተደረገ ያለው ጥረት ይጠናከራል።
ለዚህም ከኢንዱስትሪዎች የሚወገዱ ቆሻሻዎችን በአግባቡ የማስወገድ ስራ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ጠቁመው ይህንንም ለማጠናከር የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመንገባት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርና የፅዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቮች ትግበራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
በተለይም ከብክለት የጸዳ አካባቢን ለመፍጠር በተደረጉ ጥረቶች እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን ለማስፋት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በሆሳዕና ከተማ የምስጋና ዱቄት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ደመቀ በበኩላቸው ፋብሪካው ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ በማስወገድ አካባቢውን ከብክለት ለመጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለስኬቱም የተረፈ ምርት ማስወገጃን የማዘጋጀትና ምድረ ግቢውን በአረንጓዴ ልማት የመሸፈን ተግባር መከናወኑን አስረድተዋል።
ፋብሪካው በጤና ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል ከብክለት የፀዳ አካባቢን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በወራቤ ከተማ የአበሩስ ዱቄት ፋብሪካ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ነስሬ ናቸው።
ፋብሪካው ለፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ሴፍቲ ታንክን በመጠቀም ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመዋል።
በቀጣይም ፋብሪካው ንፅህናው የተጠበቀ ምርትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ የማድረግ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልል ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።