ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የሁለት ሀገራት አምባሳደሮችን አሰናበቱ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፡- የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የሉክሰምበርግ አምባሳደር ዣን ክራውዘር እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አምባሳደር መሐመድ ሳሌም አልራሺዲን አሰናብተዋል።

በሀገራቱ መካከል ያለው ፍሬያማ እና ስኬታማ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል።


 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ተሰናባቿ በኢትዮጵያ የሉክሰምበርግ አምባሳደር ዣን ክራውዘር፤ በቆይታቸው የሀገራቱን የዲፕሎማሲ ትብብር የሚያጠናክሩ ሥራዎችን መስራታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያና ሉክሰምበርግን የኢኮኖሚ ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተከናወኑ ተግባራትም ስኬታማ እንደሆኑ አንስተዋል።

በዚህም የፋይናንስና ኢኮኖሚ ሙያተኞችን አቅም የሚያጎለብት የስልጠና መርሃ ግብር በመቅረጽ በሁለቱ ሀገራት ውጤታማ የልምድ ልውውጥ መደረጉን አስረድተዋል።


 

የሀገራቱ ጠንካራ ወዳጅነት ወደፊትም በአረንጓዴ ኢኮኖሚና በፋይናንስ ልማት የትብብር ዘርፎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሉክሰምበርግ ኩባንያዎችን ቀልብ በመሳብ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሉክሰምበርግ ኩባንያዎችም የኢትዮጵያን የገበያና የኢንቨስትመንት አማራጭ የለውጥ ሂደት በመመልከት ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም