የስፖርት ዲፕሎማሲን ማስተዋወቅ ያለመ የዲፕሎማቶች የእግር ኳስ ውድድር በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ዲፕሎማሲን ማስተዋወቅ ያለመ የዲፕሎማቶች የእግር ኳስ ውድድር በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፦ አራተኛው የዲፕሎማቶች የእግር ኳስ ውድድር ቅዳሜ ሰኔ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ይከናወናል።
ውድድሩን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዩናይትድ ኪንግደም፣ካናዳ እና ሜክሲኮ ኤምባሲዎች ጋር በመተባበር ነው።
የፌዴሬሽኑ እና የኤምባሲዎቹ ተወካዮች ስለ ውድድሩ አላማ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጡ ይገኛሉ።
በውድድሩ ላይ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ከ30 በላይ ኤምባሲዎች፣ የዲፕሎማሲ ሚሲዮኖች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አጋሮች ይሳተፋሉ።
ውድድሩ የስፖርት ዲፕሎማሲ ለማስተዋወቅ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የባህል ልውውጥን ማጠናከር ዓላማ መሆኑ ተመላክቷል።
ውድድሩ ቅዳሜ ሰኔ 6 ቀን 2018 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚካሄዱ ሲሆን፥ በዕለቱም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኤምባሲዎችንና ድርጅቶችን የወከሉ 25 የእግር ኳስ ቡድኖች ይወዳደራሉ።
በውድድሩ ላይ ከ2 ሺህ 500 በላይ ታዳሚዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከእግር ኳስ ውድድሩ በተጨማሪ የተለያዩ ሁነቶች እንደሚካሄዱ ተመላክቷል።
ውድድሩን በመጠቀም የዲፕሎማሲ፣ የንግድ እና የፖለቲካ አጋርነቶችን ለማጠናከር ታልሟል።
ውድድሩ የአዲስ አበባን የዓለም አቀፍ ግንኙነት ወሳኝ ማዕከልነቷን ይበልጥ እንደሚያጎላ በመግለጫው ላይ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ለውድድሩ ዝግጅት ድጋፍ እንዳደረጉም ተመላክቷል።