ቀጥታ፡

የኃይል አቅርቦትን አስተማማኝነትና ዘላቂነት ለማረጋገጥ የፀሃይ ሃይል ልማትን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቷል

አዳማ፤ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፡-የኃይል አቅርቦትን አስተማማኝነትና ዘላቂነት ለማረጋገጥ የፀሃይ ሃይል ልማትን ለማስፋፋት ትኩረት መሰጠቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ አማራጭ የኃይል ምንጮችን ለማስፋፋትና በዘርፉ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎን ለማጠናከር ያለመ የውይይት መድረክ በአዳማ በማካሄድ ላይ ይገኛል ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) እንደገለፁት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች።

በተለይ በውሃ፣ በፀሃይ፣ በንፋስና በጂኦተርማል ሃይል ልማት ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸው 
በአሁኑ ወቅት 96 በመቶ የሚሆነው የሃይል አቅርቦት ከኃይድሮ ኤሌክትሪክ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ አስተማማኝና ዘላቂ የሃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ አማራጭ የሃይል ልማት የማስፋፋት ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ከአማራጭ ታዳሽ ሃይል ልማት የፀሃይ ሃይል ልማት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ልማቱ ላይ የግሉን ዘርፍና ባለድርሻ አካላትን ለማሳተፍ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችና አሰራሮች መዘርጋታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የፀሀይ ኃይል ልማቱ አርሶና አርብቶ አደሮች በመስኖና በተለያዩ የስራ መስኮች በዘላቂነት እንዲሳተፉና ህይወታቸው እንዲለወጥ በማድረግ ረገድ ቁልፍና አጋዥ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዋና የሃይል መስመር ርቀው የሚገኙ ወረዳዎችና የገጠር ቀበሌዎችን የመብራት ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ ብሎም በመስኖ ልማት እንዲሳተፉ ጭምር ውጤት እየተገኘበት ነው ብለዋል።


 

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዩ.ኤን.ዲ.ፒ አፍሪካ ሚኒግሪድ ፕሮግራም ማኔጀር አቶ ይመስላል ተፈራ በበኩላቸው የግሉ ዘርፍ በፀሃይ ሃይል ልማት እንዲሳተፍና ዘርፉ በትብብር እንዲለማ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይ ከህግ ማዕቀፎች ጀምሮ በርካታ የአሰራር ማሻሻያዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው የሃይል ዘርፉ አንዱ የኢንቨስትመንት መስክ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይ በግብርና ዘርፍ ብቻ የተወሰኑ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች በጸሃይ ኃይል ልማት በመሳተፍ ገበያ ተኮርና የገቢ አቅማቸውን የሚያሳድግ ሰፋፊ የግብርና መስኖ ልማት እንዲያከናውኑ ዕድልን የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም ፕሮግራሙ ለህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች በጸሃይ ኃይል ልማት ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና ከመስጠት ባለፈ በፓይለት ደረጃ በሐዋሳ፣ ሶማሌና ቄለም ወለጋ ዞኖች እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።


 

በኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የኢነርጂ አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ሶሬሳ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በታዳሽ ሃይል ልማት ማስፋፋት ላይ  በትኩረት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በተለይ በቄለም ወለጋ ላሎ ቂሌ ወረዳ የሚኒግሪድ የፀሃይ ሃይል ልማት ለማከናወን በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በተጨማሪም የክልሉ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች በፀሃይ ኃይል ልማት እንዲሳተፉ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም