በሲዳማ ክልል ለሀገር አቀፍና ክልል አቀፍ ፈተናዎች ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ለሀገር አቀፍና ክልል አቀፍ ፈተናዎች ዝግጅት ተደርጓል
ሀዋሳ፤ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ለሀገር አቀፍና ክልል አቀፍ ፈተናዎች አስፈላጊ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሳ ገለጹ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ የተደረገውን የቅድመ ዝግጅት በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አደርገዋል።
በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ 26 ሺህ 735 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እንደሚወስዱ ገልጸዋል።
በፈተናው የተማሪዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ አስፈላጊ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው፤ የትምህርት ዓመቱ ከመጀመሩ ሁለት ወራት አስቀድሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የማዘጋጀት ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
ዘንድሮ በክልሉ ከሚፈተኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 50 ከመቶ የሚሆኑት ፈተናውን በበይነ መረብ እንደሚወስዱ ገልጸው፤ ለዚህም ኮምፒውተርን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ስራ ተከናውኗል ብለዋል።
በተመሳሳይ የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል ተማሪዎችም ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ በመፈተኛ ማዕከላት ፈተናውን እንደሚወስዱ ጠቁመው፤ ይህም ኩረጃን ለመከላከል እና ምቹ የፈተና አስተዳደር ሥርዓት እንዲኖር ያግዛል ብለዋል።
በሦስቱም የትምህርት እርከኖች የሚፈተኑ የክልሉ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከመደበኛ የትምህርት ሰዓት ውጪ የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲወስዱ መደረጉን ተናግረዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ተማሪዎችን በተለያየ መንገድ በመደገፍ ዘንድሮ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ግብ ተይዞ ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
የሃዋሳ አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ትእዛዙ ባንዳው፤ በትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ከ420 በላይ ተማሪዎችን ለፈተና ሲያዘጋጁ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
መምህራን በማጠናከሪያ ትምህርት ተፈታኝ ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው፤ ሞዴል ፈተናዎችን በመስጠት ፈተናን የማለማመድ ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅተም ተማሪዎችን በበይነ መረብ ለማስፈተን የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ከማድረግ ጎን ለጎን ተፈታኞችን በስነ ልቦና የማዘጋጀት ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከሃዋሳ አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ሃሚዲ የሱፍ እና አዲስ ላቀው፤ በግላቸው ባደረጉት ጥረትና በትምህርት ቤቱ ድጋፍ ለፈተናው መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የማጠናከሪያ ትምህርት፣ ሞዴል ፈተናዎችንና በበይነ መረብ ፈተና መውሰድ የሚያስችላቸውን የቴክኖሎጂ ድጋፍ ማግኘታቸውን ገልጸው፤ በፈተናው የተሻለ ውጤት ለማምጣት መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።