ቀጥታ፡

የበጋ መስኖ ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ የአርስ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የበጋ መስኖ ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ የአርስ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቂምቢቢት ወረዳ በ21 ሺህ 463 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የመስኖ ስንዴ ሰብል ስብሰባ ተጀምሯል።


 

በዚሁ ጊዜ ምከትል ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት የበጋ መስኖ ሰብል ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያገዘ ይገኛል።

በኦሮሚያ ክልል እየተከናወነ የሚገኘው የበጋ መስኖ ልማት ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም የአርሶ አደሩን ገቢ በዕጥፍ እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።

የልማት ስራው ግብርናውን ለማሸጋገር ጭምር እያገዘ መሆኑን ጠቅሰው የግብርና ሜካናይዜሽን ግብዓቶችን በብዛት፣ በጥራት እንዲሁም ፈጠራን መጠቀም እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ኢኒሼቲቭ መልክ እየተካሄደ ሲሆን ይህም በክረምት ዝናብ ብቻ ተወስኖ የነበረው የግብርና ባህል መለወጥ እያስቻለ ነው ብለዋል።


 

በዚህ ወቅት የክልሉ አርሶ አደር በሁሉም የልማት ወቅቶች የግብርና ስራን እያከናወነ ሲሆን የገጠር ልማትን ከመሠረቱ ለመቀየር የተጀመረው ስራ ይጠናከራል ነው ያሉት።

አቶ አወሉ አብዲ አክለውም በዞኑ በትራክተር ማረስና በኮምባይነር ሰብል የመሰብሰብ ባህል እየተለመደ መጥቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም