ቀጥታ፡

የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከላት ከ230 ሺህ በላይ ተገልጋዮችን ማስተናገድ ችለዋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ስራ ከጀመረበት አጭር ጊዜ ጀምሮ ከ230 ሺህ በላይ ህዝብን ማስተናገዱን የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ማዕከላቱ 99 በመቶ የተገልጋዮች እርካታን ማስመገባቸውንም አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና ለአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተወጠነው ይህ አዲስ መሶብ ፕሮጀክት ታላቅ ስኬት እያስመዘገበ እንደሚገኝ አመልክቷል።


 

እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 11 ማዕከላትን ለመክፈት ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፣ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ዘጠኙ ማለትም አራዳ፣ ቦሌ፣ ልደታ፣ ቂርቆስ፣ አዲስ ከተማ፣ ጉለሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ እና የካ ሙሉ በሙሉ ወደ አገልግሎት ማስገባት ተችሏል።

የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ ተረፈ (ኢ/ር) እንደገለጹት፣ ቀሪዎቹ የአቃቂ እና የለሚ ኩራ ማዕከላት የግንባታ አፈጻጸማቸው ከ99 ነጥብ 5 በመቶ በላይ በመሆኑ በቀጣይ ቀናት ተመርቀው አገልግሎት መጀመር የሚያስችላቸው ዝግጅት ተጠናቅቋል።


 

ማዕከላቱ ስራ ከጀመሩበት አጭር ጊዜ ጀምሮ ከ230 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ያስተናገዱ ሲሆን፣ በተደረገው ዳሰሳም የተገልጋዮች እርካታ 99 በመቶ መድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

ይህ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው በከተማ አስተዳደሩ ልዩ ድጋፍ የባለሙያ ቅጥር፣ ስልጠና እና መሰረታዊ ግብዓቶች ቀድመው በመሟላታቸው መሆኑንም ጨምረው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም