የዲጂታል ፋይናንስና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀልን ለመከላከል ከፍትህና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ፋይናንስና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀልን ለመከላከል ከፍትህና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው
አዳማ ፤ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፦የዲጂታል ፋይናንስና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀልን ለመከላከል ከፍትህና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ኢትዮ - ቴሌኮም አስታወቀ።
"የኢትዮ ቴሌኮም እና የፍትህ ተቋማት ጥምረት ለዲጂታል ኢትዮጵያ ደህንነት" በሚል መሪ ሀሳብ በዲጂታል ፋይናንስና የቴሌኮም ማጭበርበር እንዲሁም መሰረተ ልማት ላይ እየደረሰ ባለው ጉዳትና መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ ስልጠና በአዳማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ሊጋል ኦፊሰር አቶ ለማ ተሰማ፤ በቴሌኮም ዘርፍ የተገኘውን ስኬት ለማስቀጠል ኩባንያው የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ለተግባራዊነቱ እየተጋ ይገኛል ብለዋል።።
ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ የሆኑት የቴሌኮም እና የዲጂታል አገልግሎቶች አካታች ሀገራዊ ልማትን በማፋጠን ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን አንስተው በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ቀጣይ መዳረሻ እና ዲጂታል መፃዒ ዕድል የተሳካ ለማድረግ የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በመቅረጽ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
አዲሱ ስትራቴጂ “አድማስ ዲጂታል” ኢትዮ ቴሌኮምን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እና በዲጂታል የጎለበተ ኩባንያ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸው ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎችን በማፋጠን፣ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ አዳዲስ ዕድሎችን ለመክፈት ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል።
በኩባንያው ያለፉት አመታት ስኬታማ ግስጋሴ ውስጥ የተለያዩ ተግዳሮቶች አጋጥመዋል ያሉት አቶ ለማ፤ በተለይም የዲጂታል ፋይናንስ እና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎችን ጠቅሰዋል።
በቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም ዘረፋና ስርቆትም ሌላኛው ችግር መሆኑን አንስተው እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከል በተለይም ከፍትህ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም የሕግ ጉዳዮች አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ወርቁ ታየ፤ የስልጠና መድረኩ ያተኮረው በዲጂታል ፋይናንስ ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል እንዲሁም የቴሌኮም መሠረተ ልማት ላይ የሚፈፀም ወንጀልን ለመከላከል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገሪቷ የዲጂታል ፋይናንስና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀልን ለመከላከል ከፍትህና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ከፖሊስና ፍርድ ቤቶች የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።