ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው ውስጥ 72 ከመቶ የሚሆነው መሬት በዘር ተሸፍኗል

ጋምቤላ፤ ሰኔ 3/2018(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው ውስጥ ከ72 በመቶ በላይ የሚሆነው መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ እስታወቀ።

የጋምቤላ ክልል ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ የውሃ አማራጭ እና ለተለያዩ ሰብሎች ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት ያለው በመሆኑ ለግብርና ኢንቨስትመንትም ሆነ በአነስተኛ እርሻ ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ትልቅ አቅም ያለው ነው።

በመሆኑም ክልሉ ያለውን ፀጋ በመጠቀም የክልሉን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና ክልሉ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ መጫወት የሚገባውን ሚና እንዲወጣ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆኑ ተገልጿል።




የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አንድሮው ቱት ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በተያዘው የመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው መሬት አንድም ማሳ ጦም እንዳያድር በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የተጠናከረ የንቅናቄ ስራ እየተከናወነ ነው።

በእስካሁኑ ሂደትም በምርት ዘመኑ ለማልማት ከታቀደው 180 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 130 ሺህ ሄክታሩ በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች መሸፈኑን ጠቁመው ይህም የእቅዱን 72 ከመቶ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ቀድመው ለሚዘሩ የበቀሎ፣ የሰሊጥ፣ የለውዝና ሌሎች የሰብልና የጓሮ አትክልት የተዘጋጁ ማሳዎች በዘር መሸፈናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የበልግ ዝናብን የሚጋሩት በማጃንግ ዞን የሚገኙ የጎደሬና የመንጌሽ ወረዳዎች ያለውን ምቹ ስነ-ምህዳር በመጠቀም ኩታ ገጠምን ጨምሮ የመኸር ግብርና ልማት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ቀሪውን ማሳ ዘግይተው በሚዘሩ ሰብሎች ለማሸፈንም የባለሙያዎች ስምሪት በማካሄድ የግብዓት አቅርቦትን ጨምሮ የተጠናከረ የድጋፍና ክትትል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አክለዋል።

በምርት ዘመኑ እየለማ ያለው መሬት ከቀዳሚው ዓመት በስምንት ሺህ ሄክታር ብልጫ ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህም ከ5 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ መጣሉን አቶ አንድሮው ገልጸዋል።




በጎደሬ ወረዳ ጎሽኔ ቀበሌ በኩታ ገጠም ልማት የተሰማሩት አርሶ አደር አብረሃም አባተ ከመጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ የበቆሎ ሰብል በኩታ ገጠም ማልማታቸውንና ሰብሉም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።




የግብርና ልማት በኩታ ገጠም ሲሰራ የግብርና ግብዓቶችን ለማግኘትና በሰብል ላይ ጉዳት የሚያደርሱ እንስሳትን ለመከላከል ጭምር የጎላ ጠቀሚታ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ኢቲባ ድንገታ ናቸው።

በዘንድሮው የመኸር እርሻ በኩታ ገጠም ማልማት በመጀመራቸው ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶችን በወቅቱ ማግኘት እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል

በክልሉ ማጃንግ ዞን በሚገኙ የጎደሬና መንጌሽ ወረዳዎች በኩታ ገጠም የለማ የበቆሎ ሰብል በዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ተጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም