በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከ197 ሺህ በላይ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከ197 ሺህ በላይ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሳተፋሉ
ሰቆጣ ፤ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፦በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከ197 ሺህ በላይ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚሳተፉ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የዜጎች በጎ ፈቃድ አገልግሎትና የወጣቶች ንቅናቄ ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ ሙሉጌታ ስኳር ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግሮች በመፍታት ረገድ ውጤት እየተመዘገበበት ነው።
የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠልም በመጪው ክረምት 197 ሺህ 250 ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሳተፍ 584 ሺህ 860 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።
በአገልግሎቱም 518 የአቅመ ደካማ ቤቶችን በአዲስ የመገንባትና የመጠገን፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ ምርታማነትን የማሳደግ፣ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች 17 ተግባራት ላይ እንደሚከናወን ገልፀዋል።
ከሰኔ 15/2018 ዓ/ም ጀምሮ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሳተፉ ወጣቶችን የመመዝገብ፣ የመለየትና የማዘጋጀት ስራ በማከናወን ከሃምሌ ጀምሮ ተግባሩ እንደሚጀመር አስረድተዋል።
የቅድመ ዝግጅት ስራውን ለማከናወንም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ወጣቶች ከወዲሁ ተመዝግበው ዝግጅት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
በአማራ ወጣቶች ማህበር የዋግ ኽምራ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ወንድሙ ገብረ እግዚአብሄር ወጣቶች የክረምቱን የእረፍት ጊዜ በበጎ ተግባር ላይ እንዲያሳልፉ እየተሰራ ነው ብሏል።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 377 ሺህ 360 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።