ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሀገር በቀል የአካባቢ ጥበቃ ባህልን በማጠናከር ተፈጥሮን የመንከባከብ ሥራ እየተከናወነ ነው

ዲላ፤ ሰኔ 3/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሀገር በቀል የአካባቢ ጥበቃ ባህልን በማጠናከር ተፈጥሮን የመንከባከብ ሥራ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ለውጥ ባለስልጣን ገለጸ።

በክልሉ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ቀን "ለአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ እርምጃ" በሚል መሪ ሀሳብ በአከባቢ ጽዳት፣ በችግኝ ተከላ እና በፓናል ውይይት በዲላ ከተማ ተከብሯል።

ቀኑ ስለአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ተግባራዊ እርምጃ ማጠናከርን ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።

የ‎ባለስልጣኑ ሃላፊ ግዛቴ ግጄ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የሚያስከትለውን አደጋ ለመቀነስ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ጥረት እየተደረገ ነው።

በተለይ በጌዴኦ፣ ኮንሶ፣ የኦሞ ሸለቆዎችና መሰል የክልሉ አካባቢዎች በሀገር በቀል የአካባቢ ጥበቃ ባህል ዓለም አቀፍ እውቅና እንዳላቸው አንስተው ይህንን በማጠናከር ተፈጥሮን የመንከባከብ ሥራ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ አልፎም የታዳሽ ሃይል አጠቃቀምን በማሻሻል ብክለትን በመቀነሱ በኩል ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።

‎የአካባቢ ጥበቃ የጋራና የተቀናጀ ተግባራዊ ምላሽ ይፈልጋል ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ናቸው።

ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ተከላ በማከናወን ዞኑ የሚታወቅበትን ሀገር በቀል የአካባቢ ጥበቃ እውቀት ከማጠናከር ባለፈ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።

‎የዲላ ከተማ ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከአየር ንብረት ተጽዕኖ ነጻ የሆነች ከተማ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በከተማው የተከናወኑ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት እንዲሁም የችግኝ ተከላና የጽዳት ስራዎች ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መቀነስ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም