በቆሻሻ አወጋገድና መልሶ አጠቃቀም ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የአዲስ አበባን የጽዳትና የአረንጓዴ ልማት ደረጃ እያሳደጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቆሻሻ አወጋገድና መልሶ አጠቃቀም ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የአዲስ አበባን የጽዳትና የአረንጓዴ ልማት ደረጃ እያሳደጉ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2018(ኢዜአ)፦ በቆሻሻ አወጋገድ እና መልሶ ጥቅም ማዋል ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የአዲስ አበባን የጽዳት እና የአረንጓዴ ልማት ደረጃ እያሳደጉ መሆኑን የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
በተጨማሪም ለከተማዋ ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር በኩልም ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ተመላክቷል።
'ሪች ፎር ቼንጅ ኢትዮጵያ' የተሰኘ ዓለምአቀፍ ድርጅት ከአይኬኢኤ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር “የኢትዮጵያ አረንጓዴ መጻኢ ዕድል፦ በኢትዮጵያ የቆሻሻ አወጋገድ እና ሰርኩላር ኢንተርፕራይዞችን መገንባት” በሚል መሪ ሀሳብ ቆሻሻን ወደ ቢዝነስ ለመቀየር ያሰለጠናቸውን ሥራ ፈጣሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን አዲስ ሰልጣኞችም አቀባበል ተደረጎላቸዋል።
በምረቃ መርሃ-ግብሩ የተገኙት የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ እሸቱ ለማ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በከተማዋ ቆሻሻን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲቀይሩ በማድረግ በኩል አበረታች ሥራ እየተሰራ ነው።
ይህም እንደ ሀገር በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚደረገውን ጥረት በተግባር የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በቆሻሻ አወጋገድ እና መልሶ ጥቅም ማዋል ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የአዲስ አበባን የጽዳት እና የአረንጓዴ ልማት ደረጃ ከማሳደግ ባሻገር ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር በኩል ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱም መሰል ስራ ፈጣሪዎችን እና የፈጠራ ሃሳቦችን በፖሊሲ፣ በማበረታቻ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በማስተሳሰር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የ'ሪች ፎር ቼንጅ ኢትዮጵያ' ካንትሪ ዳይሬክተር መቅድም ጉልላት በበኩላቸው፤ ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለሚደረገው ሽግግር ቀጣይነት ያለው የፈጠራ ሥራ፣ ትብብር እና ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሥራ ፈጣሪዎች የአካባቢ ጥበቃ ተግዳሮቶችን የሚፈቱ ተግባራዊ መፍትሄዎችን በማዘጋጀትና ለማህበረሰቡ ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድሎችን በመፍጠር በኩል ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።