ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቀጣናዊ ደህንነትን በማረጋገጥ በትብብር ላይ የተመሰረተ የጋራ ዕድገትን ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቀጣናዊ ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ በትብብር ላይ የተመሰረተ የጋራ ዕድገትን እንደሚፈጥር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና ምሁር ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ከዓለም ጋር የምትገናኝባቸው የብዝሃ ባሕር በርና የባሕር ዳርቻ መዳረሻ ወደብ ባለቤት እንደነበረች በታሪክ ተሰንዶ ይገኛል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ላይ የተፈጸመው በደል የሚያስቆጭ ነው።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ መነሳቱም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የህዝብ ቁጥርና የደኅነነት ስጋቶችን መቀልበስ የሚስችል ትብብር ከማጎልበት የሚመነጭ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ለውጡም ለበርካታ ዓመታት በህዝብ ልብ ተዳፍኖ የቆየውን ታሪካዊ፣ ፍትሐዊ፣ ሕጋዊና መልክዓ ምድራዊ የባህር በር ባለቤትነት ግልጸኝነት መፍጠሩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሰላማዊ፣ ሕጋዊና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ተከትሎ መቅረቡም ዓለምአቀፍ ቅቡልነትና ምክንያታዊነት ማጉላቱን አስረድተዋል።

በቀጣይም ቀጣናዊ ደህንነት፣ ዓለምአቀፍ ስምምነቶችን፣ በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ ድርድር አቅምን በማጎልበት ለጥያቄው ምላሽ ማስገኘት እንደሚገባ መክረዋል።

ዜጎችም የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት በተለያዩ አማራጮች ለዓለምአቀፍ ማህበረሰብ በማስገንዘብ ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ቀጣናዊ ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ የጋራ ዕድገትና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ትብብር እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ መከላከያ ኮሌጅ ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር አየለ በከሪ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔና ሃያልነት ከነበራት የባህር በር ባለቤትነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ሕጋዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ተፈጥሯዊ የባሕር በር ባለቤትነትም ከቀይ ባሕር፣ ገልፍ ኦፍ ኤደን እና ሕንድ ውቅያኖስ ጋር ጭምር የተሰናሰለ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት ተዳፍኖ የነበረው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ መነሳቱም ኢትዮጵያን ከስልጣኔና ሃያልነቷ የማስታረቅ ብሔራዊ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም