ቀጥታ፡

የ816 ምርጫ ክልሎች ውጤቶች ወደ ማዕከል ገብቶ የማረጋገጥ ስራ እየተከናወነ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2018(ኢዜአ)፦ ከሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ክልሎች መካከል የ816 ውጤቶች ወደ ማዕከል ገብቶ የማረጋገጥ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ ገለጹ።

ከዚህም መካከል የ24 የምርጫ ክልሎች ውጤቶች በቦርዱ ተረጋግጠው መጽደቃቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ማካሄዱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ በሰጡት መግለጫ በዛሬው እለት በወታደራዊ ካምፖች እና መጠለያ ጣቢያዎች የተካሄደው ልዩ ምርጫ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።

ሰብሳቢዋ ምርጫ ከተካሄደባቸው 1ሺህ 139 ምርጫ ክልሎች ውስጥ ከሁለቱ ምርጫ ክልሎች በስተቀር በሁሉም የጊዜያዊ ውጤት መለጠፉን ገልጸዋል።

በሀላባ አንድ እና በቀብሪ በያ ምርጫ ክልሎች ከምርጫ ጣቢያዎች ቦታ ርቀት የተነሳ የመደመር ስራ በምርጫ ክልል ደረጃ አለመጠናቀቁን ገልጸዋል።

እስከ አሁን ባለው ሂደት የ816 ምርጫ ክልሎች ውጤት በማዕከል ደረጃ የማረጋገጥ ስራ እየተከናወነ ሲሆን፤ የ24 ምርጫ ክልሎች ውጤት መጽደቁን አስታውቀዋል።

የ501 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች ላይ ከተካሄደው ውስጥ 353 በማዕከል ደረጃ መግባቱን ገልጸው፤ በክልል ምክር ቤት ከ638 የምርጫ ክልሎች ውስጥ 463 ወደ ማዕከል መግባቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም