ቀጥታ፡

በ442 ወታደራዊ ካምፖች እና በ82 መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ዜጎች ዛሬ ድምጻቸውን ሰጥተዋል - ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2018(ኢዜአ)፦ በ442 ወታደራዊ ካምፖች እና በ82 መጠለያ ጣቢያዎች ለመራጭነት የተመዘገቡ ዜጎች ዛሬ ድምጽ መስጠታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ማካሄዱ ይታወቃል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ በዛሬው እለት በወታደራዊ ካምፖች እና መጠለያ ጣቢያዎች የተካሄደውን ምርጫ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ቦርዱ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በመደበኛው ጠቅላላ ምርጫ በልዩ ሁኔታ ላልተሳተፉ ዜጎች የድምጽ መስጫ ቀን እንደሚያመቻች ገልጸዋል።

ቦርዱ ለዚሁ የሚሆን ልዩ የምርጫ ጣቢያ በማዘጋጀት የተለያዩ ስራዎችን ማከናወኑን ጠቁመዋል።

ለአስፈጻሚዎች እና ለአስተባባሪዎች ስልጠና መስጠቱን ገልጸው፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጉንም ተናግረዋል።

ምርጫውን ለማካሄድም በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች በትላንትናው እለት የምርጫ ቁሳቁስ ሙሉ በሙሉ መቅረቡን ተናግረዋል።

በካምፖች በመራጭነት የተመዘገቡ ዜጎች ዛሬ ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ድምጻቸውን መስጠታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰዓትም በሁሉም ወታደራዊ ካምፖች እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ መጠለያዎች በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ሲካሄድ የቆየው ምርጫ ከአንድ ጣቢያ ውጪ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልጸው፤ በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱም ያጋጠመ ችግር እንደሌለ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም