ቀጥታ፡

አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች የስበት ማዕከልነቷን እያረጋገጠች ትገኛለች -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ከተማ የዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች የስበት ማዕከልነቷን እያረጋገጠች ትገኛለች ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ ከጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና ከአፍሪካ በሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል (Africa CDC) ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዦን ካሴያ ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።


 

ውይይታቸውም በቀጣይ ኖቬምበር ወር አዲስ አበባ 5ኛውን አለምአቀፍ የህብረተሰብ ጤና ኮንፈረንስ ለማስተናገድ መመረጧንና ኮንፈረንሱን በጋራ ለማዘጋጀት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን አንስተዋል።

አዲስ አበባ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በመሰረተ ልማት ስራዎች፣ በነዋሪዎች እንግዳ ተቀባይነት፣ ሰላሟ የተረጋገጠ ከተማ በመሆኗ እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ለማካሄድ ምቹ ከተማ መሆን መቻሏንም ገልጸዋል።

በዚህም “የአፍሪካ የጤና ሉዓላዊነት እና ደህንነትን ማላቅ በሚል 5ኛውን ዓለም ዓቀፍ የህብረተሰብ ጤና ኮንፈረንስ ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ዝግጅቶች በስፋት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡


 

ኮንፈረንሱ የሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የህብረተሰብ ጤና መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች እና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ትልቅ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም