የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አማራጮች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አማራጮች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት ዘመን አፈራሽ የቴክኖሎጂ አማራጮች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን የከተማና መሰረት ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እጅግ ዘመናዊና ፈጣን የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም የተገነቡ ቤቶችን በሚያሳይ የግንባታ ሳይት ጉብኝት አድርገዋል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በጉብኝቱ ወቅት የተገነቡ ቤቶችን የግንባታ ሂደት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መሪነት ከተሞች የብልጽግና ማዕከል እንዲሆኑ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት በአሁኑ ወቅት ወደ 76 የኢትዮጵያ ከተሞች ተደራሽ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግሥት ይፋ ያደረገውን 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶች የመገንባት እቅድ ለማሳካት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ግንባታዎችን በተለመደው መንገድ ብቻ ማከናወን የሕዝቡን የቤት ፍላጎት በፍጥነት መመለስ እንደማያስችል ጠቁመው ሚኒስቴሩ የተለያዩ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቀ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ቤቶች መገንባት የሚያስችል የ '3D Concrete Printing' (በሮቦት የታገዘ የኮንክሪት ሕንጻ ህትመት) ቴክኖሎጂ እየተተገበረ እንደሆነ አንስተዋል።
ይህ ቴክኖሎጂ የብረት ግብዓትን ወደ 30 በመቶ፣ ሲሚንቶን ደግሞ ከ35 በመቶ እስከ 40 በመቶ ገደማ መቀነስ የሚችልና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ አማራጭ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ጂ+4 ቤቶች እየተገነቡ ሲሆን ዲዛይኑ እስከ 14 ወለል እና ከዛ በላይ መሄድ የሚያስችል አቅም እንዳለው ተናግረዋል።
በተጨማሪም የብረት ተገጣጣሚ ቤቶች እና የቅድመ-ፋብሪካ ቴክኖሎጂዎች እንደ ተጨማሪ አማራጭ እየታዩ መሆኑንም አስታውቀዋል።