ቀጥታ፡

ደኅንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት ሥርዓት ለመገንባት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2018(ኢዜአ)፦ የትራፊክ አደጋን ለመከላከልና ደኅንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት ሥርዓት ለመገንባት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የኦሮሚያ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲው የመንገድ ደኅንነትን የማረጋገጥ ዓላማ በዘላቂነት ለማሳካት የሚያግዝ "ብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ" ከተሰኘ ዓለምአቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

በመድረኩ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ኃላፊ ከማል ማሜ እንደገለጹት፤ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነትን ይበልጥ ለማጠናከር ከድርጅቱ ጋር እ.አ.አ ከ2026 እስከ 2030 ድረስ በጋራ መሥራት የሚያስችል ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በአሁኑ ወቅት ይህንን ስምምነት ወደ ሙሉ ትግበራ የማሸጋገር ሥራ የተጀመረ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ በሸገር፣ በቢሾፍቱና በአዳማ ከተሞች ላይ ትኩረት አድርጎ ስኬታማ በሆነ መንገድ እየተተገበረ ይገኛል።

ከተቋሙ ጋር የሚደረገው ትብብር የመንገድ ደኅንነትን ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸውን የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን፣ የቴክኒክና የቁሳቁስ አቅርቦቶችን እንዲሁም የፋይናንስ አቅም ግንባታዎችን ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል።

የትራፊክ አደጋዎችን በጋራ ለመከላከልና ደኅንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት ሥርዓት ለመገንባት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎና ኃላፊነት ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የብሉምበርግ ግብረ ሰናይ ድርጅት የዓለም አቀፍ የመንገድ ደኅንነት ዳይሬክተር ኬሊ ላርሰን፣ ድርጅቱ በአዲስ አበባ የነበረውን ውጤታማ ተሞክሮ በመጠቀም በኦሮሚያ ክልልም በአደጋ ተጋላጭ ቦታዎች ላይ ያተኮረ የመረጃ ማሰባሰብና ትንተና ሥራን እንደሚደግፍ ገልጸዋል።


 

ይህ ተነሳሽነት በአሽከርካሪዎችና እግረኞች ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ እንደ ፍጥነት መቆጣጠሪያ፣ የመቀመጫ ቀበቶና ራስ መከላከያ አጠቃቀም ባሉ የሕግ ማስከበር ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የትራፊክ ፖሊሶችን አቅም የመገንባት ሥራ ያካትታል ብለዋል።

ድርጅቱ የመንገድ ደኅንነትን ለማስጠበቅና አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያደርገውን ዘርፈ-ብዙ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ እአአ እስከ 2030 ድረስ በኢትዮጵያ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።


 

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ከሚሆንባቸው ከተሞች መካከል የሸገር ከተማ መንገድ ትራፊክ ደኅንነት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ማሙሽ ጫላ በሰጡት አስተያየት፤ በከተማዋ አስተማማኝ የመንገድ ደኅንነትን ለማስፈን በርካታ ውጤታማና ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

በተመሳሳይ የቢሾፍቱ ከተማ የትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አበራ ሽፈራው በበኩላቸው፤ ደኅንነቱ የተጠበቀ የትራፊክ ሥርዓት መገንባት የሚያስችሉ የተለያዩ የሕዝብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በስኬት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም