ቀጥታ፡

የወልድያ ሕዝብና አመራር ለፈተና ሳይበገሩ ከተማዋን ወደ ዘመናዊ የልማት ማዕከልነት እየቀየሩ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2018(ኢዜአ)፦ የወልድያ ከተማ ሕዝብና አመራር ሰው ሠራሽ ፈተናዎችን በጽናት በመቋቋም ከተማዋን ወደ ዘመናዊ የልማት ማዕከልነት መቀየር መቻላቸውን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን የገለጹት በወልድያ ከተማ የተገነቡ ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በበቁበት መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከተማዋ የጀግኖች ታሪክ የሚዘከርባት፣ ሕብረ-ብሔራዊ ወንድምና እህት ሕዝቦች በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩባት የኢትዮጵያዊነት መገለጫ መሆኗን ገልጸዋል።


 

ከተማዋ በተደጋጋሚ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ተቋቁማ፣ በአንድ እጇ ሰላምን በሌላ እጇ ልማትን ይዛ መጓዟን አብራርተዋል።

ዛሬ የተመረቁ የልማት ፕሮጀክቶች የወልድያ ከተማን ገጽታ የቀየሩ መሆናቸውን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የጠቀሱት።

ታዳጊዎች ስለ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና ስለ ወደፊት ቴክኖሎጂ ያላቸው የእውቀት መሻት ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ ከመሆን ባለፈ ራዕይ ያላቸው ዜጎችን ለመቅረጽ እየሠራች መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

ይህ በፈተና ውስጥ ሆኖ የመሥራት ልምድ ሌሎች የክልሉ ከተሞችና ወረዳዎች ሊማሩበትና የሥራ መነሻ ሊያደርጉት የሚገባ መሆኑን በአጽንኦት ጠቅሰዋል።

ወልድያ ገና ብዙ ልማት እንደሚገባትና በአራቱም አቅጣጫዎች ለንግድ ምቹ የሆነ ስትራቴጂካዊ አቀማመጧን ታሳቢ ያደረገ ጉዞን ማፋጠን እንደሚገባም አንስተዋል።

በሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ የተገነባው ዘመናዊ ስታዲየም ከፍተኛ እድሳት እንደሚፈልግና ከተማዋን የስፖርትና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ለስታዲየሙ የሚመጥኑ ዘመናዊ ሆቴሎች ሊገነቡ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የከተማዋን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ከተቻለ ከዚህ የላቀ ልማት ማምጣት እንደሚቻልም ገልጸዋል።


 

​የወልድያ ከተማ ከንቲባ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው፤ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ፅዱ ማድረግ ያስቻሉ አስደናቂ የልማት ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

የወልድያ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም የከተማዋ ነዋሪዎች ፈጣን የመንግሥት አገልግሎት የሚያገኙበትን ምኅዳር የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።

በልማት ፕሮጀክቶች ምረቃ መርሃ ግብሩ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም