የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ አቻው ጋር ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም የወዳጅነት ጨዋታውን ያከናውናል።
ዓለም አቀፍ የወዳጅነት መርሐ ግብሩ ብሔራዊ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ ከዛምቢያ ጋር ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ዝግጅት የሚያግዝ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ጨዋታው ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።
አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ ከዛምቢያ ጋር ለሚደረገው ወሳኝ ጨዋታ ዝግጅት ትናንት ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል።
ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ነገ በካፍ የልህቀት ማዕከል በመሰባሰብ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጀምሩ ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዛምቢያ ጋር የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ጨዋታውን ሰኔ 27 እና ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ያደርጋል።
ኢትዮጵያ በድምር ውጤት ካሸነፈች በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ታልፋለች።
10ኛው የፊፋ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።