ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ዕዳዎቿን እያራገፈች ተስፋዎቿን እየጨበጠች ወደፊት እየገሰገሰች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ ፤ሰኔ 2 /2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ዕዳዎቿን እያራገፈች ተስፋዎቿን እየጨበጠች ወደፊት እየገሰገሰች ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወልድያ ከተማ የተገነቡ ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶችን መርቀው ለአገልግሎት ከፍተዋል።


 

በምረቃው ወቅትም እንደገለጹት የተመረቁት የልማት ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ወደፊት የመገስገስ ጉዞ የሚያሳዩና የኢትዮጵያን ዕድገት ማንም ሊያስቆመው እንደማይችል ማረጋገጫዎች ናቸው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወልድያ ከተማ ሕዝብ ጽንፈኝነትንና ከፋፋይነትን በመቃወም የሚታወቅ፣ ምርጫው ሰላምና ጠንካራ መንግሥት መሆኑን በየጊዜው ማሳየቱን ገልጸዋል።

መንግሥት ትግሉ ከተወሰኑ አካባቢ ሽፍቶች ጋር ሳይሆን መንገዳቸውን ክፍፍልና ድህነት ካደረጉ ቆሞ ቀር ኃይሎች ጋር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት ያረጀ አስተሳሰብ ይዘው የቆሙ አካላት የሀገሪቱን ፈጣን ጉዞ መገንዘብ እንዳልቻሉም አስረድተዋል።

በጫካ ያሉ አካላት የኮሪደር ልማትን፣ የሌማት ትሩፋትን፣ የገበታ ፕሮጀክቶችንና የስንዴ አብዮትን የመሰሉ በሀገሪቱ የመጡ ታላላቅ ለውጦችን ለማየት እንዳልታደሉ ገልጸዋል።

በከተሞች የሚካሄደው የኮሪደር ልማት የውበት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከተሞችን የማዘመንና የሕዝብን የኑሮ ደረጃ ከፍ የማድረግ ዓላማ በማንገብ በመስፋፋት ላይ ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ከተሞች ፉክክር ከምሥራቅ አፍሪካና ከዓለም ከተሞች ጋር መሆን እንዳለበት የገለጹ ሲሆን፤ አገልግሎትን ለማዘመንም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ እየተስፋፋ መሆኑን ጠቁመዋል።

በወልድያ ከተማ የተገነቡት የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት፣ የዲጂታል ቤተ መጻሕፍትና የሳይንስ ካፌዎች ትውልዱን ከዕለት መረጃ ወደ ጥልቅ ዕውቀትና ምርምር የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የገበያ ማዕከላትና የሱቆች ፕሮጀክቶች የንግድ እንቅስቃሴን በማሳለጥ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውና በሌማት ትሩፋት አማካኝነትም በምግብ ራስን የመቻል ጉዞው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ዕዳዎቿን እያራገፈችና ተስፋዎቿን እየጨበጠች መጓዟን እንደምትቀጥል የገለጹት አቶ ተመስገን፣ ጠላት ቢሰበሰብ የሀገሪቱን ጉዞ ማደናቀፍ እንደማይችል አጽንኦት ሰጥተዋል።


 

የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ወደ ገጠር ጭምር በማስፋፋት የሀገሪቱን ብልጽግና እውን ለማድረግ መንግሥት፣ ባለሃብቱና ሕዝቡ በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም