ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በወልድያ ከተማ የልማት ፕሮጀክቶችን መረቁ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በወልድያ ከተማ የልማት ፕሮጀክቶችን መረቁ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2 /2018 (ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በወልድያ ከተማ የልማት ፕሮጀክቶችን ዛሬ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ የኢትዮጵያ ጉዞ ወደፊት ነው። ጠላት የፈለገውን ያህል ቢያቅድ ከጉዟችን እንደማያስቆመን ወልድያ ምስክር ናት ብለዋል።
ዛሬ በታሪካዊቷ፣ በየጁዎች ሥልጣኔ መገኛ በሆነችው ወልድያ ከተማ በመገኘት፣ አመራርና ሕዝብ በአንድነት ተግቶ ያሳካቸውን የልማት ፕሮጀክቶች መመረቃቸውን ገልጸዋል።
ወልድያ የልማት፣ የፅናትና የድል አምባ ናት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተማዋን የማዘመን፣ የኮሪደር ልማትን የማስፋፋት፣ የሕዝብና የዲጂታል ቤተ-መጻሕፍትን የመገንባት እንዲሁም የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከላትን እውን የማድረግ ሥራዎቻችን ወደፊት የመገስገሳችን ማረጋገጫዎች ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
መንገዳችን መደመር፣ ግባችን ደግሞ ብልጽግና ነው! ትግላችን መንገዳቸውን ክፍፍል፣ ግባቸውን ድህነት ካደረጉ ቆሞ-ቀሮች ጋር በመሆኑ የኢትዮጵያን ልዕልና ሳናረጋግጥ አንቆምም ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
ሺህ ጠላት ቢሰበሰብ የኢትዮጵያን ጉዞ ለአፍታም እንደማያስቆመው አስገንዝበዋል።