ቀጥታ፡

የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት ደንብ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው 

አዲስ አበባ፤ሰኔ 2 /2018 (ኢዜአ)፦የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት ደንብ የግብርና ኢኮኖሚ ሽግግርን በማሳለጥና የገጠር ልማትን በማጎልበት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ታዜር ገብረእግዚአብሔር ገለጹ፡፡ 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት ደንብ ቁጥር 589/2018 ዓ.ም ዙሪያ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።


 

ይህ ሥርዓት አርሶ አደሮች፣ ማኅበራትና አቀናባሪዎች ደረጃውን የጠበቀ ምርት በመጋዘን አስቀምጠው በደረሰኝ አማካኝነት የባንክ ብድር የሚያገኙበት አሠራር ነው።

አሠራሩ አርሶ አደሮች በምርት መሰብሰቢያ ወቅት የሚገጥማቸውን የገንዘብ ዕጥረት ለመቅረፍ በኢትዮጵያ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አማካኝነት ተግባራዊ ሆኗል።

ቀደም ሲል አርሶ አደሮች በገንዘብ እጥረት ምርታቸውን በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ ይገደዱ የነበረ ሲሆን፣ ይህም በምርታማነትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።

አዲሱ አሠራር ግን አርሶ አደሮች ምርታቸውን በደረሰኝ በማስያዝ ብድር እንዲያገኙና በተሻለ ዋጋ በመሸጥ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ ያስችላቸዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ታዜር ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት፤ ሥርዓቱ የገጠርና የግብርና ልማት ሽግግርን በማፋጠን አስተማማኝ የፋይናንስ አቅርቦት ዕድል የሚፈጥር ነው።

ሥርዓቱ ከ20 ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም ግልፅ ተቆጣጣሪ ባለመኖሩ የቆየ ሲሆን፣ አሁን ግን መንግሥት በሕግና መመሪያ ባለቤት በማበጀት ተግባራዊ አድርጎታል ብለዋል።

አርሶ አደሮች ምርታቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ በማከማቸት ብድር ማግኘት እንዲሁም መቼና እንዴት መሸጥ እንዳለባቸው የማሰቢያ ጊዜ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

ሥርዓቱንም በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር እንዲሆን በማስቻል የፋይናንስ ተቋማትን የሚያበረታታ ደንብ፣ መምሪያና የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱን አስረድተዋል።

የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ይኼነው ዘውዴ (ዶ/ር) የደረሰኝ ሥርዓቱ የአርሶ አደሮችን ድካም የሚመጥን የተሻለ ገበያና ዋጋ ማግኘት የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

አሠራሩ ምርታማነትን በማሻሻል፣ በተመዘገበ መጋዘን ለሚቀመጥ ምርት በደረሰኙ የብድር ዋስትና የሚያገኙበትን ዕድል በመፍጠር የአርሶ አደሮችን የመደራደር አቅም ያሳድጋል ብለዋል።

የብድር መስፈርቶች የአርሶ አደሮችና ማኅበራትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ማድረግ እንዳለባቸው የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ሥርዓቱ የአርሶ አደሩን ሕይወት በመቀየር የግብርና ሽግግርን ያሳካል ብለዋል።

አግራ ግብርናን ለማዘመን ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በ15 ሀገራት እየሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ለኢትዮጵያ የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት ውጤታማነትም በትብብር እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አምቢሳ ፤የዕዳ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት ደንብ ለባንኮች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡


 

አርሶ አደሮችና ህብረት ሥራ ማህበረት የብድር ማስያዣ ችግር ይገጥማቸው እንደነበር ገልጸው፤ ባንኮች የደረሰኝ ሥርዓቱን ብቻ በመያዝ ብድር ማቅረብ ይችላሉ ብለዋል፡፡

የአማራ ባንክ የብድር ክፍል ኃላፊ እሸቴ የማታ፤ በበኩላቸው ባንኮች የዕዳ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓቱን እንደ ብድር ምርት ማድረጋቸው በአርሶ አደሮችና ባንኮች መካከል መተማመንን ይፈጥራል ብለዋል፡፡


 

የዕዳ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት ደንብ ለባንኮች አስተማማኝ የማበደር ዋስትና እና ለአርሶ አደሮች ደግሞ እፎይታን እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም